ትኩረት የነፈግናቸው የሃሜት ሰበቦች
~
ሃሜት ፀያፍ እንደሆነ የምናምንበት ግን በተግባር መራቁ የሚያቅተን ክፉ ባህሪ ነው። ለሃሜት የሚዳርጉን ሰበቦች ብዙ ናቸው። ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው:-
1- የተቅዋ ማነስ፦
አንድ ሰው በልቡ ውስጥ አላህን መፍራት ሲቀንስ የሚናገረውን መመዘን ይቀራል። በንግግሩ ሳቢያ የሚመጣበትን ጣጣ ከማሰብ ይልቅ የሚሰማውን ሁሉ መናገር ደስታ ይሰጠዋል። ስለዚህ በዚህ በሽታ የተጠቃ ሰው (ያልተጠቃ አለ ግን?) ህክምና የሚፈልግ ከሆነ ልቡን ከማከም ይጀምር። ተቅዋውን ይፈትሽ።
2- ምቀኝነት፦
ሌላኛው የሃሜት ሰበብ በሌሎች ላይ የሚኖረን የምቀኝነት ስሜት ነው። "እኔ ከዚህ በሽታ ንፁህ ነኝ" እያልክ ራስህን አትሸንግል። ምቀኞች ምቀኝነታቸውን አያምኑም። የራስ እንትን አይገማም ይባላል። ስለዚህ ሃሜተኝነት የሌላ በሽታ ማለትም በምቀኝነት የመጠቃት ምልክት ሊሆን ስለሚችል ደጋግመህ ልብህን አዳምጥ። ከዚያም በተቅዋ ታከመው።
3- ውሎ:-
ሌላኛው የሃሜት ሰበብ ጓደኛ ነው። ሰው ብቻውን በሃሜት አይለፈልፍም። ሃሜት ላይ አድማጭ፣ አጃቢ፣ አጋዥ፣ ... ትልቅ ሚና አላቸው። ሃሜት ላይ የምትወድቀው ከማን ጋር ስትሆን እንደሆነ አንዴ በአይነ ህሊናህ ተመልከት። ከማን ጋር ሆነው ሰው የምታማው? ከዚያም ችግሩን ለመፍታት ከልብህ አስብበት። ተነጋግሮ ችግሩን ለመፍታት መፍትሄው ከራቀ ለሰበቡ ያለህን ቅርበት ቀንስ። ያን ካላደረግክ ከነ ህመምህ ልትኖር ወስነሃል።
4- ራስን ማጉላት:-
ሌላኛው የሃሜት መንስኤ ሌሎችን በማሳነስ ወይም በማጠልሸት ራስን የማጉላት ድብቅ ፍላጎት ነው። ይሄ ከሃሜቱ ልክፍት በፊት ልንታከመው የሚገባ ሌላ በሽታ ነው። አዎ ብዙ የሃሜት ገፊ ምክንያቶች ውስጥ ከጀርባ ያደፈጡ ራስን በሆነ ነገር ልዩ የማድረግ ወይም የመስቀል አባዜ ስለሚኖር ነፍሲያችንን ምን ፈልጋ ከሃሜት ሰፈር እየተልከሰከሰች እንደሆነ ቀስ ብለን እንከታተላት። ምናልባት እጅ ከፍንጅ ልንይዛት እንችላለን።
5- ቀልድና ቧልት:-
ብዙ ጨዋታዎች የሞቁ የደመቁ የሃሜት ድግሶች ናቸው። በቀልድ እያዋዛን የምንዘለዝለው የሃሜት ቁርጥ ለጊዜው ጣእሙ ልዩ ሊሆን ይችላል። ሰው ሳያውቅ የሰውን ስጋ አጣጥሞ ቢበላ ላይደንቅ ይችላል። የሚገርመው እያወቅን ደጋግመን መቀጠላችን ነው። ሃሜት የሰው ስጋ መብላት ነው። ያውም የሞተን ሰው አካል! ምን ስሜት ይሰጣል?
{وَلَا یَغۡتَب بَّعۡضُكُم بَعۡضًاۚ أَیُحِبُّ أَحَدُكُمۡ أَن یَأۡكُلَ لَحۡمَ أَخِیهِ مَیۡتࣰا فَكَرِهۡتُمُوهُۚ وَٱتَّقُوا۟ ٱللَّهَۚ}
"ከፊላችሁም ከፊሉን አይማ። አንደኛችሁ የወንድሙን ስጋ የሞተ ሆኖ ሊበላው ይወዳልን? (መብላቱን) ጠላችሁትም፤ (ሐሜቱንም ጥሉት)። አላህንም ፍሩ።" [አልሁጁራት፡ 12]
Ibnu Munewor
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor