"ዓቂቃ"
አቂቃ ማለት አዲስ ለተወለደ ህፃን ልጅ የሚታረድ መስዋእት
የሚደረግ እርድ ነው። የተወደደ እና የተፀና የተከበደ ነቢያዊ ፈለግ
እርድ ነው።
“ዐቂቃ ማረድ በጣም የጠበቀ እና የተወደደ ሱና (ሱና ሙአከዳ)
ነው።
ምክንያቱም ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል
"ማንኛውም ልጅ በ7ኛው ቀን በሚታረድለት ዐቂቃ የተያዘ ነው ።
ይህም ማለት ዐቂቃ የሚታረድለት ሕፃን ለወላጆቹ በቂያማ ቀን
ሸፈዐ ይሆናል ።ስሙ የሚወጣለትም ራሱንም (ፀጉሩን)
የሚላጨው በዛን ዕለት ነው።" ሲሉ መናገራቸውን ነው
(አቡዳውድ እና ነሳኢ) ዘግበውታል።
የዐቂቃ ዓላማው (የተደነገገበት) ምክንያት ለአላህ ሱብሃነሁ
ወተዓላ ምስጋና ለማድረስ ነው። ይህም አንድ ሰው ልጅ
ስለተወለደለት በመደሰት በ 7ኛው ቀን ደስታውን ለመግለፅ እና
ይህንንም ደስታውን ሰዎች እንዲያውቁት ለማድረግ እና
የተወለደውም ልጅ የማን እንደሆነ ለማሣወቅ ነውና አላህ ደግሞ
ልጁን እንደሚጠብቀው፣ሷሊህ ልጅ እንዲሆንለት ምክንያትም
እንዲሆነው የሚደረግ አርዶ ሰውን የማብላት ስርኣት # አቂቃ
ይባላል።
በአብዛኞቹ ሙስሊም ምሁራን እንዳሉት ዐቂቃ መደረግ ያለበት
ትልቅ ሱና (ሱና ሙአከዳ) ነው። እንደ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ
ዐቂቃ ማድረግ ዋጅብ (ግዴታ) ነው የሚሉ ዑለማዎችም አሉ።
በላጩና የተመረጠው የዐቂቃ ማውጫ ጊዜም ልጅ በተወለደ
በሰባተኛው (7ኛው) ቀን ነው የሚሆነው።
☞ ወላጆች (እናትና አባት) አሊያም አያቶች ማለትም የወላጅ
አባት እና እናት ለልጃቸው አሊያም ለልጅ ልጃቸው ዐቂቃ
ማውጣት አለባቸው፣ይችላሉም።
የተወለደው ልጅ ወንድ ከሆነ ሁለት በግ(ፍየል) ሴት ከሆነች
ደግሞ 1 በግ(ፍየል) ሊታረድ ይወደዳል ።
ምክንያቱም ነብዩ ሙሐመድ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም የአሊይ(ረዐ)
ልጅ ሐሰን በተወለደበት ጊዜ ሁለት በግ አርደዋል ።
(ቲርሚዚ ዘግበውታል)
እንዲሁም ስሙን ደህና ኢስላማዊ ስም በመምረጥ ሊጠራው
ይገባል።
ለምሳሌ ወንድ ከሆነ አብዱረህማን, አብዱላህ፣ሙሀመድ ወዘተ
....... ሴት ከሆነችም ደግሞ አሲያ፣ መሪየም፣ ኸዲጃ፣ ፈጢማ
ወዘተ......ብሎ ስም ቢያወጣላቸው ይወደዳል።
ሰባተኛው ቀን ያልታረደ እንደሆነ በ14ኛው ቀን ሊታረድ ይችላል
ያም ካልሆነ በ 21ኛው ቀን ቢያወጣ ችግር የለውም ይላሉ
ኡለማዎች፣
በአጠቃላይ አንድ ልጅ እስኪጎረምስ ድረስ አቂቃ ማውጣት
ይችላል የሚሉ ኡለማዎችም አሉ፣ እናም ቀኑ አልፎዋል ብለን
ይህን የጠበቀና የተወደደ የረሱል(ሰአወ) ሱና ከመተግበር
አንዘናጋ።
ምን አልባት ህፃኑ ሰባት ቀን ሳይሞላው የሞተ እንደሆነ ዐቂቃ
ማረዱ አስፈላጊ አይሆንም ብለዋል ኡለማዎች።
አንድ ሰው በህፃንነቱ ወላጆቹ አቂቃ ካላወጡለትና ትልቅ ሰው
ከሆነ በሁዋላ ና አቅሙ ካለው ጓደኞቹን ሰብስቦ አላማውን
ነግሯቸው(ዐቂቃ እንደሆነ ነግሯቸው) አቂቃ ማውጣት ይችላል
ብለዋል።( ኢብን ባዝ ረሂመሁላህ)
ስለዚህ እድሜያችን የፈለገ ያህል ቢሆንም አቂቃን ነይተን
ማውጣት እንችላለንና አንዘናጋ
የታረደው እንሠሣ ሥጋው በዒድ አል-አድሃ በዓል እንደሚደረገው
ሁሉ ሦስት ቦታ መከፈል አለበት። አንድ ሦስተኛው- ለድሃ፣ አንድ
ሦስተኛው- ለጓደኞች እና አንድ ሦስተኛው ደግሞ ለቤተሰብ
ይሠጣል።
አንድ ሰው የታረደውን ሥጋ ሁሉንም ለድሆችና ችግረኛ ሰዎች
መስጠት ይችላል።
ልጆች የአላህ ስጦታ ናቸው። እናም ይህን ታላቅ ፀጋ የሠጠንን
አላህን ማመስገን ይኖርብናል። ልጆችንም ገና ከህፃንነታቸው
ጀምሮ ልንንከባከባቸውና በኢስላማዊ አስተዳደግ እና ትምህርት
ያድጉ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ልናደርግላቸው ይገባል።
አላህ (ሱወ) ሷሊህ ልጆችን ይወፍቀን 🤲