~አቶ ፉላን ሆይ! ሴት ልጅ በአንገትህ ላይ የታሠረች አማና መሆኗን አስታውስ፣ በየጊዜው ያንን አማና አድስ፣እንደዋዛ በቀላሉ አትበጥስ።
ደግሞም ያ ቀን ትዝ ይበልህ፣ማለቴ በዕድሜ ካንተ የምታንሰዋን ያቺን ቆንጆ ልጅ…ወላጆቿ እጆቿን ይዘው ላንተ ያስረከቡበትን ቀን፣ትልቅ ነው፣ በሳል ነው፣ቁምነገረኛ ነው፣ያስብላታል፣ ይንከባከባታል፣አይበድላትም…ብለው ከአላህ በታች አንተን አምነው፣ የአብራካቸዉን ክፋይ ልጅን ያህል ትልቅ ነገር አንስተው ሠጡህ፣አዎ ልጅን ያህል ግዙፍ ነገር ማን እንደዋዛ አንስቶ ይሠጣል ወዳጄ!
~እናማ…አማናዉን በቀላሉ አትየው፤ጊዜው ረዝሟል ብለህ አደራዉን አታጣጥለው፤
አታራክሰው አታናንቀው፤ ወንድ ሁን እስቲ በአላህ! ድሮ ወንድነት አማናን በመጠበቅ ደረጃ ነው የሚለካው አሉ፤የተሠጠህን አማና በአግባቡ ያዝ።እሷም እኮ ላንተ ብላ ብዙ መስዋእትነት ከፍላለች፣ ስንቶች በዓለማዊ ጥቅሞች እየደለሏት፣ ስንቱ ቆንጂ፣ ስንቱ ሀብታም እየተከተላት … እኩያዬ ነው፤ እንገነዛዘባለን፣ እንተሳሰባለን ብላ …ልቧን ከፍታ እሺ ብላ፣እየተተቸች እየተሰደበች፣እጇን ለእጅህ ሠጠች፣ አንገቷን ከደረትህ አዋለች፣ ከብዙ ወንዶች መካከል አንተን መረጠች፣ይሄ በራሱ አላህን የምታመሰግንበት ትልቅ ፀጋ ነው፣
የሚወዱትን ማግኘት፣ካፈቀሩት ጋር መኖር፣
ያኔ ለዚህ በመታደልህ እንኳን ደስ ያለህ ያሉ ብዙዎች ነበሩ። ታዲያ አንተሳ የጥንት መሻቷንና ፍላጎቷን፤ሀሳቧንና ምኞቷን፣ እንዴት ማሳካት አቃተህ በረቢ! እስቲ ወንድ ሁንማ በጌታ…ቤትህ ላይ ዙሪያ መለስ ወንድ ሁን፣እዝነት፣ ጥንካሬ፣ ፍቅር፣ለስላሳነት፣ ትሁትነት፣ ክብር፣መታወቂያ መለያህ ይሁን፣ወንድነት ኩስትርና አይደለም፣
ወንድነት ሻካራነትና ድምፅ መጎርነን አይደለም፣ወንድነት ሴትን ልጅ መምታት አይደለም፣ወንድነት ሴትን ልጅ ማስለቀስ አይደለም፣ወንድነት ሀሳቧን መናቅ በአስተያየቷ መሳቅ አይደለም፣ወንድነት በሴት ልጅ ሞራልና ክብር ላይ መረማመድ አይደለም፣
√ባለፈውም ወንድ ሁን ብየህ ነበር፤አሁንም ወንድ ሁን ነው ያልኩህ!