ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ - ረሒመሁላህ - ሲሞቱ ጊዜ ታስረውበት በነበረው ወህኒ ቤት ውስጥ በሳቸው የእጅ ፅሑፍ የተፃፉ እንዲህ የሚሉ አሳዛኝ የግጥም ስንኞች ተገኝተዋል። በግርድፉ ተርጉሜዋለሁ።
“እኔ ነኝ ደካማው ከጃይ … ከሰማያቱ ባለቤት
በሁለመናዬ ስንኩል … እኔው ነኝ ምስኪኑ ማለት።
እኔው ነኝ የራሴ ጠላት … ነፍሴ እራሷ ነች በዳዬ
ኸይር ሁሉ የሚገኘው … ከሱ ብቻ ነው ጌታዬ።
ለራሴ እንኳን የማልሆን … የማላቀርብ አንዳች ፋይዳ
መከላከል አይሆንልኝ … በክፉ እንዳልጎዳ።
ሌላ ፈጣሪም የለኝ … ከሱ ውጭ ‘ሚያስተናብር
አማላጅም አይኖረኝ … ወደ ጌታ የሚያሻግር
በሱ ፈቃድ ቢሆን እንጂ … በፈጠረኝ በረሕማኑ
የሰማያቱ ባለቤት … እንዳወሳው በቁርኣኑ
ቅንጣት የሌለኝ ከንቱ … ያለ ጌታዬ ይሁንታ
አንዳች ተጋሪም የለው … በየትኛውም ሁኔታ
አጋዥ አይፈልግ ደጋፊ … ረዳት አይሻ የኔ ጌታ
ልክ እንደሚያስፈልጋቸው … ለወልዮቹ አይነታ።
ችግር ድህነት አርማዬ … የኔ ቋሚ መገለጫ
መብቃቃቱ የጌታ ነው … የሁልጊዜ ባለብልጫ
አንጋጣጭ ነው ወደ ጌታ … ፍጡር ሲባል ጠቅላላ
ሁሉም ተዋርዶ ይቀርባል … ቢሻው ጠላ ቢሻው ደላ።
ከፈጠረው ጌታ ውጭ … ምኞት ፍላጎት የሚሻ
ቂል፣ በዳይ፣ አረመኔ … አጋሪ ነው መጨረሻ።
ይመስገነው ፈጣሪዬ … አለሙን በፀጋው የሞላ
ላለፈውም ለመጪውም … ላደረገልን በመላ።
ከዚያም ሶላቱ ይትረፍረፍ … በምርጡ ነቢያችን ላይ
የፍጡራን ቁንጮ አይነታ … የሁሉ ላይ የላይ በላይ።” [አልዑቁድ፡ 391]
=
* ቴሌግራም ቻናል፡- https://t.me/IbnuMunewor
* ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/Ibnu.....Munewor?mibextid=ZbW
* ዋትሳፕ፦ https://whatsapp.com/channel/0....029VaA3X1e5kg7BlsJbo
* ኡማ ላይፍ፦ https://ummalife.com/IbnuMunewor