Translation is not possible.
🚀 THE GRAND COMEBACK: REWRITING DESTINY (ታላቁ ትንሳኤ፡ ታሪክን የመቀየር ጥበብ)
════════════════
▣ መግቢያ፡ የጨዋታው ግማሽ ክፍል (Half-Time Analysis)
ህይወት እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ናት። የመጀመሪያው አጋማሽ (First Semester) መጠናቀቅ የጨዋታው ፍጻሜ አይደለም። በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤቱ አላማረም ማለት ተሸንፈሃል ማለት አይደለም። አሁን ያለንበት ጊዜ ስልት ቀይረን፣ ጉልበት አድሰን ለሁለተኛው ዙር "የሞት ሽረት" ትግል የምንዘጋጅበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ትላንትናችሁ የዛሬ ማንነታችሁን አይወስንም፤ ነገን የመወሰን አቅሙ ግን አሁን ባላችሁ እጅ ላይ ነው።
 
➲ የተስፋ ብርሃን - ከዜሮ መነሳት ይቻላል!
ባለፈው መንፈቀ ዓመት ውጤታችሁ አላማረም? ደረጃችሁ ዝቅ ብሏል? "ተስፋ የለሽ ነኝ" የሚለውን የሰይጣን ሹክሹክታ አትስሙ። በእስልምና ተስፋ መቁረጥ የለም። አንድ ሰው ምን ያህል ወንጀል ቢሰራ በንስሃ (ተውበት) እንደሚመለስ ሁሉ፣ አንድ ተማሪም ምንም ያህል ቢወድቅ በቁርጠኝነት (Azim) ታሪኩን መቀየር ይችላል። ዛሬ ላይ "ዜሮ" ብትሆኑ እንኳን፣ በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት በእውነተኛ ተጋድሎ (Jihad of Education) ወደ "ጀግና" መቀየር ትችላላችሁ።
"ሰውም ለርሱ የሠራው እንጂ ሌላ የለውም፡፡ ሥራውም ወደ ፊት ይታያል (ይፋ ይወጣል) ..." (ሱረቱ አን-ነጅም፡ 39-40)
 
 
❓ የነፍስ መመርመሪያ፦ ባለፈው ሴሚስተር ውጤቴ እንዲበላሽ ያደረገው ዋናው "ቫይረስ" ምንድን ነው? እንቅልፍ? ስልክ? ወይስ ጓደኛ? ዛሬ ይህንን ቫይረስ ከስሩ ለመንቀል ለአላህ ቃል ትገባለህ?
 
➲ ለ6ኛ እና ለ8ኛ ክፍል ተማሪዎች
እናንተ በሚኒስትሪ ፈተና አፋፍ ላይ ያላችሁ ተማሪዎች ሆይ! ይህ ሰዓት "የህይወት አቅጣጫ መቀየሪያ ወሳኝ ምዕራፍ" ነው። ጊዜው እየሮጠ ነው፤ ቀልድ ያብቃ! ይህ ፈተና ከክፍል ወደ ክፍል ማለፊያ ብቻ ሳይሆን፣ የነገ ማንነታችሁ መሰረት የሚጣልበት ነው። አሁን የምታፈሱት ላብ፣ ነገ የምታለቅሱትን እንባ ያድናል። እናንተ ልዩ "ሚሳኤል" ሁኑ፤ ኢላማችሁን (ውጤታችሁን) እስክትመቱ ድረስ ወደ ኋላ አትይዩ።
ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡- "አምስት ነገሮች ከመምጣታቸው በፊት በአምስት ነገሮች ተጠቀም፡ ... ሽምግልና ሳይመጣብህ በወጣትነትህ፣ መታመም ሳይመጣብህ በጤንነትህ..." (አል-ሐኪም ዘግበውታል፡ ሶሒሕ)
 
❓ የነፍስ መመርመሪያ፦ የቀሩት ወራት በጣም ጥቂት ናቸው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ መጽሐፍትን ሸፍኖ ለመጨረስ የምትችለው በምን አይነት ፍጥነት ብትጓዝ ነው? እቅድ አለህ ወይስ በዘፈቀደ ነው የምትነጉደው?
 
➲ ምክንያት ድርደራን መቅበር (No More Excuses)
"መምህሩ አይገባኝም"፣ "መብራት ይጠፋል"፣ "መጽሐፍ የለኝም"... እነዚህ የደካሞች መዝሙር ናቸው። አላህ እርዳታውን የሚልከው ሰበቡን አድርሰው ለሚታገሉ ነው። ጠንካራ አማኝ መብራት ሲጠፋ ሻማ ያበራል፤ መምህሩ ካልገባለት ሌላ መንገድ ይፈልጋል።
ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡- "ጠንካራ አማኝ ከአላህ ዘንድ ይበልጥ የተወደደና ከደካማ አማኝ የተሻለ ነው..." (ሶሒሕ ሙስሊም)
 
 
❓ የነፍስ መመርመሪያ፦ እኔን ወደ ኋላ እየጎተተኝ ያለው "ሰበብ" ምንድን ነው? ይህንን ሰበብ ዛሬውኑ አሽቀንጥሬ ለመጣል ዝግጁ ነኝ?
 
➲ የዲጂታል እስር ቤት (ስልክና ሶሻል ሚዲያ)
ብዙ ተማሪዎችን እየገደለ ያለው "ቲክቶክ" እና "ጌም" ነው። በሁለተኛው ሴሚስተር ስልካችሁን "የሚቆጣጣራችሁ" ሳይሆን "አገልጋያችሁ" አድርጉት። ለትምህርት ካልሆነ በስተቀር ከስልክ ራቁ። የፌስቡክ ላይክ ውጤት አያመጣም፤ የቲክቶክ ቪዲዮ የወደፊቱን ህይወት አይገነባም።
 
❓ የነፍስ መመርመሪያ፦ በቀን ስንት ሰዓት በስልክ ላይ ታቃጥላለህ? ይህንን ሰዓት ለሂሳብ ወይም ለእንግሊዝኛ ብትሰጠው ኖሮ አሁን የት ትደርስ ነበር?
 
➲ የክፍተት ትንተና (Gap Analysis)
ሁለተኛው ሴሚስተር አዲስ ቤት ለመሥራት ብቻ ሳይሆን፣ የፈረሰውን ለመጠገን ጭምር ነው። ባለፈው የከበዳችሁ ትምህርት የትኛው ነው? ያንን ሳትጠግኑ ወደ ፊት መሄድ አትችሉም። ድክመታችሁን አውቃችሁ መድፈን የብልህ ተማሪ ምልክት ነው።
 
➲ ወላጆች - የቤት ውስጥ መሪዎች
ውድ ወላጆች! ልጆቻችሁ የነገ ተስፋዎቻችሁ ናቸው። በዚህ ወሳኝ ሰዓት ቤታችሁ "የፊልም ቤት" ሳይሆን "የንባብና የዱዓ ቤት" መምሰል አለበት። ከቴሌቪዥን ሪሞት ይልቅ የመጽሐፍ ገጾች ይቅረቡ። ልጆቻችሁ ሲያጠኑ አበረታቷቸው፣ ሲደክሙ አበርቱአቸው። የልጆቻችሁ ውጤት የጋራ ፕሮጀክታችሁ ነው። በዱዓ እና በክትትል ከጎናቸው ቁሙ።
 
➲ ሶላትና ስኬት - የማይነጣጠሉ ቅንጣቶች
ከአላህ ጋር የተጣላ ሰው የትምህርት ቤት ውጤቱ ቢያምርም በህይወቱ ሰላም የለውም። ጥናታችሁን ከሶላት ጋር አጣምሩ። ሶላቱን በወቅቱ የሚሰግድ ተማሪ፣ ጊዜው በረካ ይሆንለታል። የአላህ እርዳታ (ተውፊቅ) የሚገኘው በሱጁድ ውስጥ ነው። ያለ አላህ እርዳታ የሚመጣ ውጤት የለም።
"...አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለን (ጸጋ) በነፍሶቻቸው ያለን (ሁኔታ) እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥም..." (ሱረቱ አር-ረዕድ፡ 11)
 
❓ የነፍስ መመርመሪያ፦ ለአላህ ሳትሰግድ ለፈተና ብቻ የምታደርገው ጥረት ፍሬ ያፈራል ብለህ ታስባለህ? ስኬትህ ከሰላትህ ጋር እንደተሳሰረ ታውቃለህ?
 
➲ ማጠቃለያ - ብዕሩ በእጅህ ነው!
ታሪክህ ገና አልተጻፈም፤ ብዕሩ በእጅህ ነው። ሁለተኛው ሴሚስተር ባዶ ነጭ ወረቀት ነው። በዚህ ወረቀት ላይ የውድቀት ታሪክ ትጽፋለህ ወይስ የድል አድራጊነት ዜና? ምርጫው ያንተ ነው። ተነሳ! አቧራህን አራግፍ! አንተ ከተቀየርክ ዓለም አብራህ ትቀየራለች።
 
በቀጣዩ ሴሚስተር በደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ እንገናኝ! አላህ ጥረታችሁን ይባርክ፤ ልፋታችሁን በስኬት ያክልላችሁ (ያብቃላችሁ)! 🚀
 
✍️ በረሻድ ኢብኑ ሙዘሚል
════════════════
👇 Share 👇
 
Telegram: t.me/SharpSwords1
 
Tiktok: tiktok.com/@sharpswords1
 
Ummalife: ummalife.com/ReshadMuzemil
 
LinkedIn: linkedin.com/in/reshad-muzemil-139b97320
image
Send as a message
Share on my page
Share in the group