UMMA TOKEN INVESTOR

Followings
0
No followings
1 year Translate
Translation is not possible.

አብዮተኛዋ ታጋይ እና የፍልስጥኤማዊያን ትግል

እነሆ በሰላም፣ በእኩልነት እና በሰው ልጆች ነፃነት የሚያምነው የዓለም ህዝብ በሙሉ ስለሚያደንቃት ፍልስጥኤማዊት ልናወጋ ነው። ይህቺ የነፃነት ታጋይ በእስራኤልና በአሜሪካ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ "አሸባሪ" ተብላ ተፈርጃለች። የአውሮጳ ህብረትን ጨምሮ አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት ግን "የነፃነት ታጋይ" በማለት ነው የሚገልጿት። በዚህም የተነሳ በአውሮጳ ፓርላማ ተጋብዛ ንግግር ለማድረግ ችላለች።

እኛም በታጋይነቷ ነው የምናውቃት። ይህቺ ሴት ማን ነበረች? እስቲ በአጭሩ እንተዋወቃት።

የፍልስጥኤም የነፃነት ትግልን ከጀመሩት አንጋፋ ድርጅቶች መካከል አንዱ Pupolar Front for the Liberation of Palestine (PFLP) ይባላል። ይህንን ድርጅት የመሠረቱት ዶክተር ጆርጅ ሀበሽ እና ዶክተር ዋዲ ሃዳድ ነበሩ። ጆርጅ ሀበሽ የግንባሩ ዋና ጸሐፊ ሲሆን ዋዲ ሀዳድ ደግሞ የግንባሩ ወታደራዊ እና የደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ነበር።

የPFLP አመራር በተመሠረተበት ጊዜ ትኩረት ካደረገባቸው ነገሮች አንዱ ትግሉን ለዓለም ህዝብ ማስተዋወቅ ነው። በዚህም መሠረት ታጋዮቹ በ1968 ባካሄዱት የአውሮፕላን ጠለፋ የፍልስጥኤማዊያንን ትግል ለማስተዋወቅ እንደረዳ ተገንዝቧል፡፡

የግንባሩ አመራር በቀጣዩ ዓመት (1969) ከመጀመሪያው ጠለፋ በበለጠ ሁኔታ ብዙዎችን ሊያነጋግር የሚችል ኦፕሬሽን እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ የግንባሩ የወታደራዊ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ የነበረው ዶ/ር ዋዲ ሀዳድም እንዲያ ዓይነቱን ኦፕሬሽን እንዲያስፈጽም በግንባሩ የፖለቲካ ቢሮ መመሪያ ተሰጠው፡፡ ለኦፕሬሽኑ የሚያስፈልገው የፋይናንስ፣ የማቴሪያል እና የሰው ኃይል ግብአቶችም ተመደቡለት፡፡

ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ከፖሊት ቢሮው የተሰጠውን ትእዛዝ በሚያስፈጽምበት መንገድ ዙሪያ የተለያዩ አማራጮችን ሲያጠና ቆየ፡፡ በሀሳቡ የመጡትን ርእዮች ሁሉ ከገመገማቸው በኋላ አንድ ብልሃት የተሻለ ሆኖ ታየው፡፡ ይህም ጠለፋው በሴት ታጋይ እንዲመራ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከቀዳሚ የግንባሩ አባላት አንዷ የነበረችውን የሃያ አምስት ዓመት ወጣት ኦፕሬሽኑን በኃላፊነት እንድታካሄድ መረጣት፡፡ ሌሎች ሶስት ታጋዮችንም በረዳትነት መደበላት፡፡

በአራቱ ፍልስጥኤማዊያን እንዲጠለፍ የታዘዘው ነሐሴ 28/1969 ከሮም ተነስቶ በአቴንስ በኩል ትራንዚት አድርጎ ወደ ቴል አቪቭ የሚበር አንድ የእስራኤል አየር መንገድ አውሮፕላን ነበር፡፡ ወጣቶቹ ሮማ ደርሰው ለኦፕሬሽኑ መዘጋጀት ሲጀምሩ ግን የPFLP የደህንነት ኮሚቴ ያልተጠበቀ መረጃ ደረሰው፡፡ ይህም መረጃ “በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ይስሐቅ ራቢን የበረራ ቁጥሩ 840 በሆነ የአሜሪካው TWA አየር መንገድ አውሮፕላን ነሐሴ 28/1969 ከኒውዮርክ ተነስተው ሮም ይገባሉ፣ በማግስቱ ደግሞ በተመሳሳይ አውሮፕላን ወደ ቴል አቪቭ ይበራሉ” የሚል ነበር፡፡

ሚስተር ይስሐቅ ራቢንን ብዙዎች የሚያስታውሱት በ1993 ከያሲር አረፋት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ በመሆናቸው ነው፡፡ በቀደመው ዘመን ግን ሰውዬው እንዲያ አልነበሩም፡፡ ፍልስጥኤማዊያን የተጨፈጨፉባቸውንና ከሀገራቸው የተባረሩባቸውን ዘመቻዎች ከመሩት የእስራኤል የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለስልጣናት አንዱ ነበሩ፡፡ በ1948 እስራኤል ምዕራብ እየሩሳሌምን ከፍልስጥኤሞች የነጠቀችበትን ዘመቻ የመሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡ በ1967 በተካሄደው የዐረብ-እስራኤል ጦርነት ፍልስጥኤም በእስራኤል ሙሉ በሙሉ በተወሰደችበት ወቅት ደግሞ የእስራኤል የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ነበሩ፡፡ የጦር ኃይሉ በፍልስጥኤማዊያን ላይ ልዩ ልዩ ግፎችን እየፈጸመ ከሀገራቸው እንዲያባርራቸው የተሰጠውን ትእዛዝ በበላይነት ያስፈጸሙት እርሳቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህም ነበር የPFLP አመራር መረጃው ሲደርሰው እርሳቸውን አፍኖ ለመውሰድ የወሰነው፡፡

ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ከላይ የጠቀስኩት መረጃ ሲደርሰው ቀደም ብሎ ባወጣው ፕሮግራም ላይ ለውጥ ለማድረግ ወሰነ፡፡ ወደ ወጣቶቹ ደውሎም የመጀመሪያው እቅድ መሰረዙን ነገራቸው፡፡ ለትራንዚት በሮማ ከተማ በሚያርፈው የTWA አውሮፕላን ወደ ቴል አቪቭ ለመጓዝ የሚያስችላቸውን ቲኬት እንዲገዙና አውፕላኑን ጠልፈው ወደ ደማስቆ እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡

ወጣቶቹም ትእዛዙን በመቀበል በTWA አውሮፕላን ለመብረር የሚያስችላቸውን ቲኬት ገዙ፡፡ ነሐሴ 29 ቀን 1969 ጓዛቸውን ይዘው በሮማው የሊኦናርዶ ዳቪንቺ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኙ፡፡ ወደ TWA አውሮፕላን ከገቡ በኋላም ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ለአርባ ደቂቃዎችም በዝምታ ተጓዙ፡፡ አውሮፕላኑ ወደ አድሪያሪቲክ ባሕር ሲጠጋ ግን በጉያዎቻቸው የያዟቸውን ሽጉጦች በማውጣት የጠለፋ ኦፕሬሽኑን ጀመሩ፡፡

ወጣቷ ፍልስጥኤማዊት አንድ ጓዷን አስከትላ በፍጥነት ወደ አብራሪዎች ክፍል ገባችና ፓይለቱ አውሮፕላኑን ወደ ደማስቆ እንዲያበርረው አዘዘችው፡፡ ሁለቱ ወጣቶች ደግሞ የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ባሉበት ሆነው ጉዞአቸውን እንዲቀጥሉ ነገሯቸው፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም አንዲት ሴት በአውሮፕላኑ የድምጽ ማጉያ መሳሪያ እንዲህ ስትል ተደመጠች፡፡

“ጤና ይስጥልን መንገደኞች! ይህ አውሮፕላን ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ በፍልስጥኤም ህዝባዊ ነፃነት ግንባር ታጋዮች ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ የፍልስጥኤም ህዝባዊ ነፃነት ግንባር በፅዮናዊያንና በኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ሉዓላዊነቷ የተገፈፈውንና ህዝቡ የተበተነባትን ፍልስጥኤምን ነፃ ለማውጣት የሚታገል ድርጅት ነው፡፡ ግንባራችን ከፍልስጥኤም ህዝብ ጠላቶች በስተቀር ሰላማዊ ሰዎችን የማጥቃት ዓላማና ፍላጎት የለውም፡፡ ይህ አውሮፕላን የተጠለፈው የኢምፔሪያሊስት ጠላቶቻችን ንብረት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ በወዳጅ ሀገር ካረፈ በኋላ በነፃ ትለቀቃላችሁ፡፡ እስከዚያው ግን ከወንበሮቻችሁ ሳንትንቀሳቀሱ ጉዞአችሁን እንድትቀጥሉ በጥብቅ እናስታውቃለን”

ወጣቷ ይህንን የተናገረችው በእንግሊዝኛ እና በዐረብኛ ቋንቋዎች ነው፡፡ ይህች ወጣት ትግሉን የተቀላቀለችው በአስራ አምስት ዓመቷ ነው፡፡ ከላይ የተገለጸውን ጠለፋ እስፈጸመችበት ጊዜ ድረስም የትግሉ ንቁ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የPFLP አባል ሆና ዘልቃለች፡፡ ፍልስጥኤማዊያን ሴቶች በትግሉ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ በሚወሳበት ጊዜም በቅድሚያ የምትጠቀስ የትግል አርአያ ለመሆን በቅታለች፡፡

ታዲያ ወጣቷ የምትወሳው በታጋይነቷ ብቻ አይደለም፡፡ በታሪክ ምዕራፍ የመጀመሪያዋ ሴት የአውሮፕላን ጠላፊ ሆና የተመዘገበች በመሆኗም ሚሊዮኖች ያውቋታል፡፡ በዘመኑም ጉድ ተብላ ወሬዋ በብዙዎች ዘንድ ተሰራጭቷል፡፡ ገድሏን የሚዘክሩ ብዙ ጽሑፎችና መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ታሪኳን የሚዘክሩ ፊልሞች ተሰርተዋል፡፡ በእርሷ የተነሳም በርካታ የዓለም ህዝብ ስለፍጥኤማዊያን ትግል ሊያውቅ ችሏል።

ያቺ ፍልስጥኤማዊት ወጣት በተጸውኦ ስሟ “ለይላ ኻሊድ” በመባል ትታወቃለች፡፡ ለይላ አሁንም በሕይወት አለች።

...ይቀጥላል

Follow for part 2

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group