Translation is not possible.
የጁሙዓ መልዕክት
 
🌙 የዕለታት ንጉስ፣ የሳምንቱ ፀሀይ – የውሙል ጁሙዓ!
 
ይህ መልዕክት ስለ ቀናት አለቃ፣ አላህ (ሱ.ወ) የመረጠው፣ መላእክት የሚያከብሩት፣ ሰማይና ምድር ለክብሩ የሚጨነቁለት ስለ "የውሙል ጁሙዓ" ነው። ጁሙዓ ለሙስሊም የክብር ካባ፣ የኢማን ባትሪ መሙያ፣ የናፍቆትና የሰላም ቀን ነው። የዚህን ቀን ታላቅነት በልቡ ያኖረና የሰራበት ሰው ህይወቱ በበረከት ይሞላል።
 
ክፍል 1፦ የጁሙዓ ቀን ታላቅነትና ኮስሞሳዊ ክስተቶች
ይህ ቀን እንዲሁ በዘፈቀደ የሚመላለስ ቀን አይደለም። የሰው ልጅ ታሪክ የተጀመረበትና የሚጠናቀቅበት ታላቅ ቀን ነው።
 
◆ ፀሀይ ከወጣችበት ቀናት ሁሉ በላጩ ቀን
የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የዚህን ቀን ታላቅነት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦
✅ "ፀሀይ ከወጣችበት ቀናት ሁሉ በላጩ ቀን የጁሙዓ ቀን ነው።" (ሶሂህ ሙስሊም፡ 854)
 
ክፍል 2፦ የአዳም (ዐ.ሰ) እና የጁሙዓ ቀን ጥብቅ ቁርኝት
የሰው ልጅ አባት አዳም ታሪክ ከዚህ ቀን ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በሶሂህ ሙስሊም ዘገባ እንደገለጹት አምስት ታላላቅ ክስተቶች በዚህ ቀን ተከስተዋል፦
☑️ አዳም የተፈጠረው በጁሙዓ ቀን ነው።
☑️ ጀነት የገባው በጁሙዓ ቀን ነው።
☑️ ከጀነት የወጣው (ወደ ምድር የተላከው) በዚሁ ቀን ነው።
☑️ አላህ ተውበቱን (ንስሀውን) የተቀበለበት በዚሁ ቀን ነው።
☑️ አዳም የሞተበትም በዚሁ ቀን ነው። (አቡ ዳውድ፡ 1046)
 
ክፍል 3፦ የዓለም ፍጻሜ (ቂያማ) እና የፍጥረታት ፍራቻ
ይህ ዓለም አብቅቶ ወደ ዘላለም ዓለም የምንሸጋገረው በዚህ ቀን ነው። ለምድራዊ ህይወታችን መጀመሪያም፣ ለፍጻሜውም ምልክት ነው።
✅ "በጁሙዓ ቀን እንጂ ቂያማ አትቆምም።" (ሶሂህ ሙስሊም፡ 854)
 
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አክለውም፦ "ከጂንና ከሰው ውጭ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ የቂያማን መቆም በመፍራት ከንጋት ጀምሮ ፀሀይ እስክትወጣ ድረስ ይህን ቀን አድምጠውት ያነጋሉ" ብለዋል። (አቡ ዳውድ፡ 1046)
 
ክፍል 4፦ አላህ የማለበት ታላቅ ቀን (ሱረቱል ቡሩጅ)
አላህ (ሱ.ወ) በታላቅ ነገር እንጂ አይምልም። በሱረቱል ቡሩጅ ላይ እንዲህ ይላል፦
 
> وَشَاهِدٍ وَمَشْهُودٍ
 
"በተመልካችም (ሻሂድ)፣ በተመሰካሪውም (መሽሁድ) እምላለሁ" (አል-ቡሩጅ 85፡3)
 
የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ሲያብራሩ፦ "የተመሰከረለት (መሽሁድ) ማለት የዓረፋ ቀን ሲሆን፤ ተመልካች (ሻሂድ) የተባለው ደግሞ የጁሙዓ ቀን ነው" ብለዋል። (ቲርሚዚ፡ 3339) አላህ የማለበት ቀን መሆኑ ክብደቱን ያሳያል።
 
ክፍል 5፦ አላህ ወደ ቀኑ መራን (የወፈቀን) ልዩ ራህመት
ከእኛ በፊት የነበሩ ህዝቦች ይህን ቀን ስተውታል። አላህ ግን እኛን በራህመቱ ወደዚህ በላጭ ቀን መራን።
✅ "ከእኛ በፊት የነበሩ ህዝቦች አላህ ከጁሙዓ ቀን እንዲስቱ አደረጋቸው። ለአይሁዶች ቅዳሜ ሆነላቸው፣ ለክርስቲያኖችም እሁድ ሆነላቸው። ከዚያም አላህ እኛን አመጣና ወደ ጁሙዓ ቀን መራን።" (ሶሂህ ሙስሊም፡ 855)
 
ክፍል 6፦ በቁርኣን ምዕራፍ የተሰየመለት ታላቅ ዕለት
ከቀናት ሁሉ በስሙ የተሰየመ ሱራ ያለው ብቸኛው ቀን ጁሙዓ ነው። አላህ በቁርኣኑ ለአማኞች ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል፦
 
> يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِذَا نُودِيَ لِلصَّلَاةِ مِن يَوْمِ الْجُمُعَةِ فَاسْعَوْا إِلَىٰ ذِكْرِ اللَّهِ وَذَرُوا الْبَيْعَ
 
"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በጁሙዓ ቀን ለሶላት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማወደስ (ሶላት) ሂዱ፤ መሸጥንም ተዉ። ይህ የምታውቁ ብትሆኑ ለእናንተ በጣም የተሻለ ነው።" (ሱረቱል ጁሙዓ 62፡9)
ይህ አንቀፅ ጁሙዓ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ፣ ከዱንያ ንግድና ጥቅም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የነፍስ ምግብ መሆኑን ያረጋግጣል።
 
ክፍል 7፦ ከቀብር ፈተና የመጠበቂያ ዋስትና
በዚህ ቀን ወይም ለሊት መሞት የአላህ ልዩ እዘነትና የጥሩ መጨረሻ ምልክት ነው።
✅ "ማንኛውም ሙስሊም በጁሙዓ ቀን ወይም በጁሙዓ ለሊት አይሞትም፣ አላህ ከቀብር ፈተና የጠበቀው ቢሆን እንጂ።" (ቲርሚዚ፡ 1074፣ ሼይኽ አልባኒ ሐሰን ብለውታል)
 
ክፍል 8፦ ዱዓ የሚሰማበት ወርቃማዋ ሰዓት
በጁሙዓ ቀን አንዲት ሰዓት አለች፤ ባሪያው አላህን የለመነበትን ነገር የሚሰጠው።
✅ "በሷ (በጁሙዓ ቀን) ውስጥ አንዲት ሰዓት አለች። ሙስሊም የሆነ ባሪያ ቆሞ የሚሰግድና አላህን የሆነን ነገር የሚለምን ሆኖ አይገጥማትም አላህ የጠየቀውን የሰጠው ቢሆን እንጂ።" (ቡኻሪ፡ 935፣ ሙስሊም፡ 852)
 
ብዙ ዑለማዎች ይህቺ ሰዓት ከዓስር ሶላት በኋላ ያለው የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነች ይጠቁማሉ።
 
ክፍል 9፦ ኹጥባን ማዳመጥና ዝምታን የመጠበቅ አዳብ
ኹጥባ እየተደረገ ማውራት ሰላቱን ዋጋ ያሳጣል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ ላይ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፦
 
✅ "በጁሙዓ ቀን ኢማሙ ኹጥባ እያደረገ ለጓደኛህ 'ዝም በል' ካልከው እንኳ በርግጥ ሰላምህን (አጅርህን) አበላሽተሃል።" (ቡኻሪ፡ 934፣ ሙስሊም፡ 851)
 
ክፍል 10፦ የጁሙዓ ቀን አዳብ (ሥነ-ሥርዓት)
ወደ አላህ ቤት ስንሄድ እንደ ሙሽራ ተውበን ሊሆን ይገባል፦
➤ ገላን መታጠብ (ጉስል)፦ "ወደ ጁሙዓ የሚመጣ ሰው ይታጠብ" (ቡኻሪና ሙስሊም)።
➤ ሱረቱል ካህፍን መቅራት፦ (አል-ሐኪም እና በይሀቂ)
➤ በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ ሶለዋትን ማብዛት፦ (አቡ ዳውድ)
➤ ሽቶ መቀባትና መዋብ፦ (ለወንዶች የተወደደ ነው)።
 
🤲 የጁሙዓ ልዩ ዱዓ
ያ አላህ! ያ ዛል-ጀላሊ ወል-ኢክራም!
በዚህ በተከበረው ቀን፣ በተከፈቱት የሰማይ ደጃፎች፣ በምትወዳቸው ባሮችህ ምልጃ ወደ አንተ እንጮሃለን፦
☑️ በተውሂድና በሱና አፅናን፦ ጌታችን ሆይ! ልቦቻችንን ባንተ አንድነት (ተውሂድ) ላይ፣ በተወዳጁ ነብይህ (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ (ሱና) ላይ እንደ ተራራ የፀና አድርግልን። ከሽርክ አዘቅት፣ ከቢድዓ ጥመት እኛንም ቤተሰቦቻችንንም ጠብቀን።
☑️ ሶላትን የምንጠብቅ አድርገን፦ የጀነት መክፈቻ ቁልፍ የሆነችውን ሶላትን፤ በወቅቷና በኹሹዕ የምንሰግድ አድርገን። የሙስሊሞችን ሳምንታዊ ኢድ ጁሙዓን ሁሌም የምንወፈቅ አድርገን።
☑️ ከቀብርና ከእሳት ጠብቀን፦ ያ አላህ! የቀብርን ጥያቄና ፈተና አቅልልን። መጨረሻችንን በሸሀዳ አሳምርልን። ከጀሀነም እሳት ጠብቀህ በጀነትህ አርካን።
☑️ ሰላምህን አውርድልን፦ የታመሙትን አሽር፣ የሞቱትን ማር፣ የተጨነቁትን ፈርጅላቸው። ለሀገራችንና ለሙስሊሙ ኡመት ሁሉ ሰላምህን ስጠን።
አሚን! አሚን! ያ ረብበል ዓለሚን!
 
📢 ይህንን መልዕክት ለሌሎች እናጋራው። መልካም ነገርን ያመላከተ እንደሰራው ይቆጠራል!
 
 
✍️ በረሻድ ኢብኑ ሙዘሚል
image
Send as a message
Share on my page
Share in the group