Translation is not possible.
🚢 የሕይወት መርከብ፦ የሰላት ጥሪ (ልዩ የጁሙዓ ስንቅ)
 
✅ መግቢያ
ምስጋና ለአለማቱ ጌታ ለአላህ ይሁን። ሰላት የሙስሊሙ መታወቂያ፣ የጨለማው ብርሃንና ከፈጣሪው ጋር በምስጢር የሚገናኝበት ገመድ ናት። ይህ መልዕክት በቸልተኝነት ለተዘጉ ልቦች መክፈቻ፣ ለጠፉ ነፍሶች ደግሞ ወደ ቤታቸው መመለሻ ጥሪ ነው።
 
ክፍል 1፡ ሰላት—ከሰባቱ ሰማያት በላይ የተሰጠ የፍቅር ስጦታ 🎁
➤ ሰላት እንደ ፆም ወይም እንደ ዘካ በምድር ላይ አልተደነገገችም። አላህ ነቢዩን ﷺ ከሰባቱ ሰማያት በላይ (ሲድረት አል-ሙንተሃ) ድረስ በመጥራት በቀጥታ የሰጣቸው ታላቅ አደራ ናት።
◆ ሼይኩል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ይላሉ፦
"ሰላት የልብ ምግብ፣ የነፍስ ብርሃንና ባሪያው ከጌታው ጋር የሚገናኝበት ሚዕራጅ (መወጣጫ) ናት።" ሰላታችሁን ስትተዉ፣ አላህ እናንተን ለማግኘት የዘረጋላችሁን የመገናኛ መስመር በእጃችሁ እየቆረጣችሁ መሆኑን አስተውሉ!
 
ክፍል 2፡ "ፈወይሉን!"—ሰላትን ለሚያዘገዩ የመጣ የቁርአን ሰይፍ ⚔️
➤ ሰላትን ጨርሰው ለማይሰግዱት ብቻ ሳይሆን፣ ለሚያዘገዩና ቸል ለሚሉ አላህ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
«ወዮላቸው (ወይሉን) ለሰላተኞች! ለእነዚያ ከሰላታቸው ዘንጊዎች ለሆኑት።» (ሱረቱ አል-ማዑን፡ 4-5)
 
◆ ታላቁ ሰሃባ ኢብኑ አባስ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፦
"ወይሉን ማለት በጀሀነም ውስጥ ያለ የሸለቆ ስም ነው። ምድራዊ ተራራዎች በውስጡ ቢጣሉ ከሙቀቱ ብርታት የተነሳ ይቀልጣሉ። ይህ ሸለቆ የተዘጋጀው ሰላታቸውን ያለ ወቅቱ ለሚያዘገዩ ሰዎች ነው።"
 
ክፍል 3፡ የመጀመሪያው የሂሳብ መዝገብ (የጥንቃቄ ጥሪ) ⚖️
➤ ነገ በቂያማ ቀን፣ ፀሐይ አንድ ስንዝር በቀረበችበትና ጭንቀት በነገሰበት ቀን መጀመሪያ የምትጠየቁት ስለ ሰላታችሁ ነው።
◆ ነቢዩ ﷺ በሶሂህ ሐዲሳቸው እንዲህ ብለዋል፦
"አንድ ባሪያ የቂያማ ቀን መጀመሪያ የሚጠየቀው ስለ ሰላቱ ነው። እሷ ከተስተካከለች ሌላው ስራው ሁሉ ይስተካከላል፤ እሷ ከተበላሸች ግን ሌላው ስራው ሁሉ ይበላሻል።" (ቲርሚዚ)
⚠️ የሰላታችሁ መበላሸት ማለት የሁሉም ነገር መክሰር ማለት መሆኑን አታውቁምን?
 
ክፍል 4፡ የነቢዩ ﷺ የመጨረሻው ኑዛዜ 📜
➤ የሰው ልጅ በመጨረሻ የሞት ጣር ላይ ሆኖ የሚናገረው ንግግር እጅግ ውድ ነው። ነቢዩ ﷺ ነፍሳቸው ልትወጣ ስትል፣ አንደበታቸው እየከበዳቸው ደጋግመው የተናገሩት ትልቅ አደራ ይህ ነበር፦
"ሰላት... ሰላት! በእጆቻችሁ ስር ስላሉትም አደራ (አላህን ፍሩ)።" (አቡ ዳውድ)
💔 የወደዷችሁና የታገሉላችሁ ነቢይ ﷺ በመጨረሻ ሰዓት የተናዘዙላችሁን አደራ መብላት እንዴት ያለ ክህደት ነው?
 
ክፍል 5፡ የብርሃን ብስራት—ፈጅርና አስር ✨
➤ በብርድና በድካም ወቅት ሰላትን ለሚጠባበቁ አማኞች ልዩ ሽልማት ተዘጋጅቷል።
◆ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
"በጭለማ ወደ መስጊድ ለሚጓዙት በቂያማ ቀን ሙሉ ብርሃን እንደሚኖራቸው አብስሯቸው።" (አቡ ዳውድ)
ደግሞም አሉ፦ "ሁለቱን ቀዝቃዛ ወቅቶች (ፈጅርና አስርን) የሰገደ ሰው ጀነት ገባ።" (ሶሂህ ቡካሪ)
❄️ የሌሊቱን እንቅልፍና የከሰዓቱን ስራ መስዋዕት አድርጋችሁ ለጌታችሁ ስትቆሙ፣ እናንተ የአላህ የቅርብ ወዳጆች ናችሁ።
 
ክፍል 6፡ የሊቃውንት ምስክርነት 💎
◆ ኢማሙ ሻፊዕይ እንዲህ ይላሉ፦ "አላህ ዘንድ በሰላት ከመቆም የበለጠ የሚያስከብርና ትልቅ ደረጃ የሚያሰጥ ተግባር አላውቅም።"
◆ ኢማሙ አህመድ እንዲህ ይላሉ፦ "አንድ ሰው በኢስላም ያለው ድርሻ በሰላቱ ልክ ነው። ሰላት የሌለው ሰው፣ ስሙ ሙስሊም ቢሆንም ማንነቱ ባዶ ነው።"
🌊 ሰላት ከአምስት ወቅት ወንጀል የምታነጻ ወንዝ ናት። አምስት ጊዜ ወደ አላህ የሚመለስ ሰው፣ ልቡ እንዴት በወንጀል ይቆሽሻል?
 
ክፍል 7፡ ተመለሱ—የተውባ በር አሁንም ክፍት ነው! 🚪
➤ ሞት ሳያንኳኳ፣ የቀብር ጨለማ ሳይውጣችሁ፣ "ጌታዬ ሆይ መልሰኝ" ብላችሁ ከመጮኻችሁ በፊት አሁኑኑ ተመለሱ። ሰላት የድል ቁልፍ ናት። ሰላታችሁን ካስተካከላችሁ አላህ ኑሮአችሁን፣ ትዳራችሁን፣ ስራችሁንና መጨረሻችሁን ያስተካክልላችኋል።
«ጌታችሁም አለ፡- "ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና።"» (ሱረቱ ጋፊር፡ 60)
 
✅ ዛሬውኑ ውዱእ አድርጋችሁ በጌታችሁ ፊት ውደቁ። እርሱ መሃሪና አዛኝ ነው።
 
✍️ ረሻድ ኢብኑ ሙዘሚል
image
Send as a message
Share on my page
Share in the group