Translation is not possible.
🔺ዑለማዎቻችንን እንተዋወቅ
#ክፍል2
~~~
ኢማሙ ማሊክ፡ (93-179 ዓ.ሂ)
👉ሙሉ ስማቸው ማሊክ ኢብኑ አነስ ኢብኑ ማሊክ ኢብኑ አቡ ዓሚር ይባላሉ።
በ93 ዓ.ሂ በመዲና-ሳዑዲ ዓረቢያ ከተከበሩ ቤተሰቦች ተወለዱ።
((ከፊሎቹ በ90 ዓ.ሂ ወይም በ95 ዓ.ሂ ወይም በ94 ዓ.ሂ ብለዋል።
ኢማሙ ዘሃቢይና ሌሎችም ግን በ93 ዓ.ሂ የሚለውን አስፍረዋል።))
የዘር ግንዳቸው ከየመን የተመዘዘ ነው።
አያታቸው ማሊክ ኢብኑ አቡ ዓሚር ታቢዒይ ሲሆኑ የታወቁ የሐዲሥ ዘጋቢ ናቸው።
እናታቸው አሊያህ ቢንት ሻሪክ ኢብኑ ዓብዱራሕማን አልአዝዲያህ ትባላለች።
ኢማሙ ማሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ፣
በመዲና ኢስላማዊ የሸሪዓ ህግን ለማጥናት ጽኑ ፍላጎት ስለነበራቸው ፊታቸውን ወደ ፊቂህ ትምህርት አዞሩ።
ኢማሙ ማሊክ የነብዩን ሶለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሶሐቦች ባዩና በነርሱም ላይ ከተማሩ ሶስት መቶ ያክል ታቢዒዮች ላይ ተምረዋል።
በመዲና ብዙ ህይወታቸውን 95 ያክል መሻኢኾች ላይ በመማር አሳልፈዋል።
1725 ያክል የነብዩን ሐዲሦች የያዘውን "ሙወጦእ" የተሰኘውን ታዋቂ ኪታባቸውን የዘገቡትም ከነዚሁ መሻኢኾች ነው።
✍️ኢማሙ ማሊክ፡ ዓብደላህ ኢብኑ ዑመርን ከሰላሳ አመት በላይ ካገለገለውና በአንድ ወቅት አሚረል ሙእሚኒን ዑመር ኢብኑ ኸጥጧብ ዲን እንዲያስተምር ወደ ግብጽ ልከውት ከነበረው ከናፊእ ላይ ቁርአንና ሐዲሥን ለአስር አመታት ያክል ተምረዋል።
ኢማሙ ማሊክ አንድን ሐዲሥ ውዱእ ሳያደርጉ አይዘግቡም ነበር።
ከመዘገባቸው በፊትም የእያንዳንዱን ግልሰብ ምንነት በጥልቀት ያጠኑ ነበር።
ኢማሙ ማሊክ ለ62 አመታት ያክል በማስተማርና ፈተዋ በመስጠት አገልግለዋል።
ከርሳቸው 1300 ያክሉ ሰዎች ሐዲሥን ዘግበዋል።
የኢማሙ ማሊክ ቤት የኢብኑ መስዑድ ቤት የነበረ ነው።
ከበሩም ላይ "ማሻ አላህ" የሚል ጽሁፍ ነበረበት።
ኢማሙ ማሊክ ረዝም፣ ጀግና፣ ቆራጥ፣ ትሁትና ቸር ናቸው።
አል-መንሱር ሶስት ሺህ ድርሃም ሰጥቶ ከመዲና ለቀው ወደ ባጝዳድ እንዲሄዱ ሲያዛቸው፣ እርሳቸው ግን ትዕዛዙን ነቅፈው በመዲና መቀመጥን መርጠዋል።
አል-መንሱር ለርሱ ህዝቡ ቃለ መሃላ እንዲገባ ሲያዝም፣ ይህ ቃለ መሃላ አይቻልም ብለው በቆራጥነት ሐቅን ሳይደብቁ ፈተዋ ሰጥተዋል።
ኢማሙ ማሊክ ማስተማር የጀመሩት ገና የ17 አመት ወጣት ሆነው ሳለ ነው።
#ከሸይኾቻቸው መካከል፦
—---------------------—
✔️ናፊእ
✔️ዓብደልሏህ ኢብኑ ዛቅዋን
✔️ሒሻም ኢብኑ ዑርዋህ
✔️ያሕያ ኢብኑ ሰዒድ
✔️ዓብደልላህ ኢብኑ ዲናር
✔️ዘይድ ኢብኑ አስለም
✔️ኢማም አዝዙህሪ
✔️ዓኢሻህ ቢንት ሰዒድ ኢብን አቢወቃስ
✔️ዓብደልሏህ ኢብኑ አቡበከር ኢብኑ ሃዝም
✔️ዓብዱራሕማን ኢብኑ ቃሲም
✔️ኢብራሂም ኢብኑ ዓብደልላህ አልመቅደሲይና ሌሎችም ይገኙበታል።
✍️ኢማሙ ማሊክ ዒልም የተማሩት ንጹህ፣ ዛሂድና እውነተኛ ከሆኑ ሰዎች ነው።
ዓላማህ ዙልቃኒ እና ዱላቂ የኢማሙ ማሊክ አስተማሪዎች ዘጠኝ መቶ ይደርሳሉ ብለዋል።
ኢማሙ ነወውይ ደግሞ በተሕዚቡል አማእ ላይ ዘጠኝ መቶ ይደርሳሉ፦ ከነዚህም ውስጥ ሶስት መቶዎቹ ታቢዒዮች ሲሆኑ ስድስት መቶዎቹ ደግሞ አትባዑ ታቢዒይን ናቸው ብለዋል።
👉ከተማሪዎቻቸው መካከል፦
—---------------------------
እንደ ሐፊዝ ኢብኑ ከሢርና ኢማሙ ዘሃብይ ያሉ አኢማዎች የኢማሙ ማሊክን ተማሪዎች ከብዛት አንጻር መጥቀስ አይቻልም ብለዋል።
ቃዲ ዒያድ ግን 1300 ያክሉን ጠቅሰዋል።
ሐፊዝ ዳረቁጥንይ 1000 ደግሞ ያክሉን ጠቅሰዋል።
ሐፊዝ አቡበከር ኸጢብ አልባጝዳዲይ ደግሞ 993 ያክሉን ጠቅሰዋል።
በፊት የርሳቸው አስተማሪዎች የነበሩትም በኋላ ላይ የርሳቸው ተማሪዎች ሆነዋል።
ለምሳሌ፦ ዝሁሪ አቡል አስወድ፣ ያሕያ ኢብኑ ሰዒድ፣ አቡ ሱሐይል እና ሌሎችም።
✔️ኢማሙ ሙሐመድ
✔️ኢማሙ ሻፊዒይ
✔️ዓብደልሏህ ኢብኑ ሙባረክ
✔️ለይስ ኢብኑ ሰዒድ
✔️ሱፍያነ ሠውሪ
✔️ኢብኑ ዑየይናህ
✔️ኢማሙል አውዛዒይና ሌሎችም ይገኙበታል።
👉ከስራወቻቸው መካከል፦
—------------------------
በአለም ላይ እጅጉን ታዋቂውና የተለያዩ ኮሌጆችና ዩኑቨርስቲዎች በከፍተኛ ትምህርት ኮርስነት የሚጠቀሙት ታዋቂው መጽሐፋቸው "ሙወጦእ" ነው።
ኢማሙ ማሊክ እለተ እሁድ ታመው በ84 ወይም በ86 ወይም በ87 ወይም በ90 አመታቸው፣ በ11ኛው ወይም በ14ኛው ረቢየል አወል በ179 ዓ.ሂ ከዚህች አለም በሞት ተለዩ።
በመዲና በጀነቱል ባቂዕ መቃብር ተቀበሩ።
ረሒመሁልሏህ።
ያሕያ፣ ሙሐመድና ሐማድ የተባሉ የሶስት ልጆች አባት ናቸው።
ኢማሙ ማሊክ ሲሞቱ 3300 ያክል ዲናር ለልጆቻቸው አውርሰው ነው።
የማሊኪያ መዣብ በአሁኑ ሰአት በሰሜንና ምዕራባዊ አፍሪካ፣ በቱኒስ፣ በሞሮኮ፣ በግብጽና በአልጀሪያ ይገኛል።
||
👉ታላላቅ ዑለማዎች ስለርሳቸው የተናገሩት፦
—--------
#ለዘጠኝ አመታት ያክል የኢማሙ ማሊክ ተማሪ የነበሩት ኢማሙ ሻፊዒይ ማሊክን እንዲህ ሲሉ ይገልጿቸዋል፦
"ምሁራኖች ስማቸው ሲጠቀስ፣
ማሊክ ኮከቡ ናቸው።" (“when scholars are mentioned, Malik is the star.”)
#ያሕያ ኢብኑ ሙዓይን እንዲህ ይላሉ፦
"እርሱ (ኢማሙ ማሊክ) በሐዲሥ አሚረል ሙእሚኒን ነው።"
#ዓብዱራሕማን ኢብኑ መህዲ እንዲህ ይላሉ፦
"በዚህች ምድር ገጽታ ላይ በነብዩ ሐዲሥ ዘገባ ከማሊክ የበለጠ ታማኝ የለም።"
እንዲህም ብለዋል፦
"ሱፍያነ ሠውሪ የሐዲሥ ኢማም እንጂ የሱንና ኢማም አይደለም።
አውዛዒይ የሱንና ኢማም እንጂ የሐዲሥ ኢማም አይደለም።
ማሊክ ግን የሐዲሥም የሱንናም ኢማም ነው።"
#ኢማሙ አቡ ሐኒፋ እንዲህ ብለዋል፦
"ከኢማሙ ማሊክ የበለጠ ፈጣን የሚገባው፣ ትክክለኛ መላሽና መምሮ ወሳጅ አላየሁም።"
#ኢማሙ አሕመድ እንዲህ ይላሉ፦
"የማን ሐዲሥ በልብ መያዝ (መሸምደድ) አለበት? ተብዬ ተጠየቅኩ።
እኔም የኢማሙ ማሊክ ስል መለስኩ።"
#ኢማሙል ቡኻሪ እንዲህ ይላሉ፦
"በጣም ታማኙ የዘጋቢዎች ሰንሰለት የቱ ነው? ተብየ ተጠየቅኩ፦
እኔም ከኢማሙ ማሊክ፣ ከዚያም ከናፊእ፣ ከዚያም ኢብኑ ዑመር ብዬ መለስኩ።"
✔️በዋና ዋቢነት፦
==========
#አቡ ኑዓይም፦ ሒልየቱል አውሊያእ: (6/345-392)
#አል-ዘሃቢ፦ ሲየር አላም አልኑበላእ: (7/382-437)
#ፉአድ አብዱል ባቂ፦ የሙወጦእ መግቢያ።
https://t.me/WATESiMU
Telegram: View @WATESiMU

Telegram: View @WATESiMU

فوائد : أبي لقمان فؤاد بن نغاش ስብና ካላማረ መልክ መልከ ጥፉ ነው
Send as a message
Share on my page
Share in the group