Translation is not possible.

ልጅህን አባት ያለው የቲም አታድርገው!

~

ልጆች ከአላህ የተሰጡ አማናዎች ናቸው። አማናን ባግባቡ አለመጠበቅ ነውር ነው። ዘመኑ እንደምናየው ከባድ ነው። የልጆችን ህይወት የሚያበላሹ ነገሮች በጣም በዝተዋል። የአደጋ ስጋት ሲጨምር ጥንቃቄያችን መጨመር ነበረበት። እኛ ግን ይበልጥ እየተዘናጋን ነው። በገዛ ገንዘብህ፣ እጅህ ላይ ባለው ሞባይል፣ ቤትህ ውስጥ ባለው ቴሌቪዥን ልጆችህን እያጠፋሃቸው እንዳይሆን ተጠንቀቅ። ልጅህ ልጅ ነው። የነገ ህይወቱን ሳይሆን የዛሬ ደስታውን ነው የሚያየው። ቅፅበታዊ ኩርፊያውን ፈርተህ፣ የእለት ደስታውን ብቻ እያየህ የጠየቀውን ሁሉ አትስጥ። የሚያስፈልገውን እንጂ የሚፈልገውን ሁሉ አታድርግ።

ትንፋሽ እስከሚያጣ አስጨንቀው እያልኩህ አይደለም። ግን ዛሬ ቁርኣን ካልቀራ፣ ዲኑን ካላወቀ፣ ትምህርት ካልተማረ መቼ ሊማር ነው? አባትነት ልጆችን ቆፍጠን ብሎ በስርአት ለማሳደግ ካልሆነ ምን የረባ ትርጉም አለው? አኺራውንም ይሁን ዱንያውን በተመለከተ ስለ ነገ ህይወቱ አንተ ካልተጨነቅክለት ማን ይጨነቅለት? አባትነትህ ለዚህ ካልሆነ ለምን ይሁን?

ስለ ልጅህ ስታስብ ልብሱና ጉርሱ ላይ አትቁም። ነጣ ገረጣ፣ ከሳ ኮሰሰ፣ ሳቀ አኮረፈ ላይ ብቻ አታተኩር። \"ለነገ ምን ይዟል?\" በል። ለሃላፊነት አዘጋጀው። ህይወት ከባድ ትምህርት ቤት ናት። ብዙ መውጣት መውረድ አላት። ነገ ምን እንደሚገጥመው አታውቅም። ሁሌ አብረኸው አትሆንም። ብትሆንም አቅምህ ውስን ናት። ጥገኝነትን አታለማምደው። ካንተ የተሻለ እንጂ ያነሰ እንዲሆን አትተወው። ከመስመር ወጥቶ ከሆነ በጊዜ ወደ ቦዩ መልሰው።

ይጫወት ፋታ ስጠው። ግና ቁም ነገረኝነትን አስተምረው። ያለበለዚያ አካሉ ቢያድግም ከልጅነት ስነ ልቦና አይወጣም። በሰላሳ አመቱም የሰው እጅ የሚጠብቅ ጥገኛ ይሆናል። ሌሎችን በሚጦርበት እድሜው ተዘፍዝፎ በአዛውንቶች ይጦራል። ከእህቱ እየነጠቀ ሱስ የሚያሳድድ ጅል ፈጥረት ይሆናል።

ባጭሩ ለልጅህ የእውነት አባት ሁነው። ከልብ አንፀው። መኖርህ በልጅህ አስተዳደግ ላይ ትርጉም ያለው ልዩነት ይኑረው። ልጅህን በአደብ፣ በእውቀት ተከትኩቶ እንዲያድግ ካላገዝከው በህይወት እያለህ የቲም አድርገኸዋል። የአባትን መኖር ትርጉም ነፍገኸዋል። የምታሳድገው ልጅ የቤተሰብ ማፈሪያ፣ የማህበረሰብ እዳ፣ የሃገር ሸክም ከሆነ በሃገርም በወገንም ላይ ትልቅ በደል ነው የፈፀምከው። ይሄ ህዝብ ጀርባውን ያጎበጠው ብዙ ሸክም አለበት። ሌላ ሸክም አትጨምርበት። ለራስህም ቢሆን ነገ በፀፀት እጅህን ከመንከስህ በፊት ዛሬ ሃላፊነትህን ባግባቡ ተወጣ። አባት ሁን። አባት!

=

የቴሌግራም ቻናል፡-

https://t.me/IbnuMunewor

Telegram: Contact @IbnuMunewor

Telegram: Contact @IbnuMunewor

كناشة ابن منور
Send as a message
Share on my page
Share in the group