Translation is not possible.

ዶ/ር ሙሐመድ ዿዊ አል-ዑሶይሚ ዛሬ ከነ ዶ/ር ኸሊልና ዶ/ር ሳሊም ጋር በነበረው ነድዋ ላይ ካነሳው ነጥብ መካከል፤ አንድ የሚያውቀው ሸይኽ MBC ላይ ፕሮግራም እንዲኖረው እንዳመቻቹለት ሲነግረው «እንደት ሙዚቃና ፊልም በቋሚነት በሚሰራጭበት ቲቪ ላይ ትቀርባለህ?» ስለው፤ «እነርሱ 24 ሰዓት የሚበክሉትን፤ አጋጣሞውን ካገኘኸው በ1 ሰዓት ባፈራርሰው አይሻልም ወይ?» አለኝ የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አስተላልፏል።

ባገኘኽበት አጋጣሚ ሁሉ ሰዎችን ወደ ቀጥተኛው መንገድ ምራ። እንዳውም ብዙዎቹ የጠመሙ ሰዎች እንዲህ አይነት ቦታ ላይ እንጂ መስጅድና መድረሳ አታገኛቸውምና በጎዳናውም፣ በየቲቪውም፣ በየ ማኅበራዊ ሚዲያውም ተጣራ።

በተጨማሪም ዳዕዋ ስናደርግ ጥበብና አዘኔታ የተላበስን መሆን እንዳለብን ሲናገር፤ እዛው በሃገረ ኩዌይት የሚያውቀውን አንድ አጋጣሚ አወሳ።

አንድ ሰው አባቱ ይሞትበትና በጣም ስላዘነ ለአባቱ መልካም የዋለ መስሎት ፎቶውን አሳትሞ 2 ሜትር በ1 ሜትር አድርጎ ውጭ ላይ ለጠፈው። ቤቱ ውስጥም ሳሎን ላይ በትልቁ ለጠፈው።

ከዚያ አንዱ ሊያስተዛዝነው ቤቱ ሲገባ ያንን ፎቶ አየ። ወዳውም ምንድን ነው ይህ? ሐራም! (لا تدخل الملائكة بيت فيه كلب ولا صورة) እያለ ጮኸበት። ይህን ሐዲሥ ሲናገር "ውሻና ምስል ባለበት ቤት መላኢኮች አይገቡም!" ሲል ምስል የምትለዋን ቃል ሲናገር ወደዛ ወደተለጠፈው የሰውየው አባት ምስል በእጁ እየጠቆመ ነበር።

በመጨረሻም «እኔም የእኔን አባት የጠላ መላኢካ እጠላለሁ!» የሚል ይዘት ያለው መጥፎ ንግግር ተናገረ።

ለዚህ ሰቅጣጭ ንግግር የዳረገው የዚያ የሰው የአነጋገር ለዛና ጥበብ ማጣት ነው። ይህ ሰው አባቱ ሞቶበታል፣ እንባው አልደረቀም። መልካም የሠራ መስሎት ፎቶ ለጥፏል። ይህኛው ያንን ሲያይ «ወንድሜ ሆይ! ለአባትህ መልካም ለመሥራት የምታደርገው ጥረት ጥሩ ነው። ማሻ አላህ! እርሳቸውንም አላህ ይዘንላቸው። ግን ይህ ፎቷቸውን የለጠፍከው ነገር ላንተም ለርሳቸውም አይጠቅምም። እንዳውም ወንጀል ይሆንብሃል።…» ብሎ በለዘብተኛ አገላለፅ አስረድቶት፤ ከዚህ ሥራው ይልቅ ሸሪዓው በፈቀደው መልኩ ከአንድ መልካም ልጅ ለሞቱ ወላጆቹ የሚጠበቁበትን ነገሮች ጠቁሞት ቢያልፍ፤ ሐቂቃ ሰውየው ወዲያውኑ ያንን ምስል አንስቶ ከቻለ የተባለውን ሌላ መልካም ሥራ በሠራ ነበር።

ብቻ! የምንናገረው ነገር ሐቅ መሆኑን ብቻ አንመልከት። ያንን ሐቅ ሰዎች በሚቀበሉን መልኩና ወደ ቀልባቸው በቀላሉ እንዲንቆረቆር በሚያደርግ መልኩ ማቅረባችንንም እናስተውል። አላህ ዕውቀትን፣ ጥበብን፣ እዝነትንና አስተዋይነትን ያድለን።

||

t.me/MuradTadesse

||

t.me/MuradTadesse

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group