Translation is not possible.

“ዓይኔ ለአፍታ ቢበራ ላየው የምመኘው ቁርአንን ነው“፡-የዳሊ ኩምቤ ኢማም

***************************

“ከ10 ትውልድ በፊት በመንደራችን ትኖር የነበረች አንዲት ሴት የሌላ ዓለም ፍጡር በህልሟ ተገልጦ እጅግ ብልህ እና አስተዋይ ዓይነ ስውር ልጅ እንደምትወልድ ይነግራታል፡፡

ይቺ ሴት በህልሟ እንዳየችው ፈጣሪውን የሚፈራ በሳል ዓይነ ስውር ልጅ ትወልዳለች፡፡

እኔን ጨምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረስን የእርሷ ዘሮች በሙሉ ዓይነ ስውር ነን፡፡ በመንደራችን ከሁለት ሰው ውስጥ አንዱ ዓይነ ስውር ነው”

ይህ ጭው ባለው የሰሃራ በረሃ ከዓለም ተገልለው የሚኖሩት የ’ዳሊ ኩምቤ’ መንደር ነዋሪዎች ኢማም ንግግር ነው፡፡

ልበ ብርሃኑ ኢማም ‘ቡህ’ ከመንደራቸው ነዋሪዎች ውስጥ ከፊሉ ዓይናማ ከፊሉ ደግሞ ዓይነ ስውር ሊሆኑ የቻሉት ከላይ በተረኩት የህልም ትንቢት እንጂ በሌላ አይደለም ይላሉ፡፡

በሰሃራ በረሃ እምብርት ከሞሪታኒያ ዋና ከተማ ‘ኑዋክቾት’ በ1 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ”የዓይነ ስውራን መንደር“ የዓለምን ትኩረት ስባለች፡፡

እዚህ ስፍራ ለመድረስ የበረሃውን ንዳድ ታግሶ የአሸዋውን ባህር ለሁለት ቀናት ማቋረጥ ግድ ይላል፡፡

በረሃው ከሚያጥበረብር ብርሃን ውጭ ለዓይን ወሰን የሚሆን አንዳች ተፈጥሯዊ ልምላሜ እና ሰው ሰራሽ ስልጣኔ አይታይበትም፡፡

መብራት፣ ስልክ፣ ኮምፒዩተር፣ ኢንተርኔት፣ መኪና፣ ፎቅ፣ ሆቴል፣ ቢሮ…ሁሉም የሉም፡፡

እንደነገሩ ከተሰሩት መኖሪያ ቤቶች ውጭ መንደሯ ያሏት ሁለት ትልቅ ሀብቶች አንድ መስጅድ እና አንድ መድረሳ ቤት ናቸው፡፡

ኢማሙ ውኃ እንደወርቅ የሚቆጠርባትን በርሃማዋን ሀገር ሞሪታኒያን ያጠጡት “አያቶቼ ናቸው” ይላሉ፡፡

“አላህ (ሱ.ወ) ለእኛ ከሰጠን ድንቅ ስጦታዎች ውስጥ አንዱ በዚህ ጭልጥ ያለ በረሃ ውስጥ የውኃ ምንጮች የት እንዳሉ ማወቅ ነው፡፡

ሞሪታኒያ ውስጥ ያሉ የውኃ ምንጮችን በአብዛኛው ፈልጎ ያገኘው እንደኔው ዓይነ ስውር የነበረው አባቴ ነው፡፡ አያቶቼም ውኃ የት እንዳለ የማወቅ ልዩ ጸጋ ነበራቸው”

ሌላኛዋ በስም ያልተጠቀሰች የመንደሩ ነዋሪ ፈጣሪ ግልጡን እንዳያዩ ከልክሎ ስውሩን የሚያዩበትን ረቂቅ ዓይን ልባቸው ላይ የማብራቱ እንቆቅልሽ ለእርሷም አጃኢብ የሚያሰኝ መሆኑን ትገልጻለች፡፡

እንደ እሷ ዓይነ ስውር የሆኑ ወንድም እና እህቶቿን እናታቸው እንደምትንከባከባቸው እነሱም እናታቸውን በመታዘዝ የልጅነታቸውን አጉድለው እንደማያቁ ትናገራለች፡፡

“የመንደሯን መንገዶች የቤቴን ያህል አውቃቸዋሁ፡፡ መስኪድ ለመሄድ፣ ውኃ ለመቅዳት እና ሌሎች ጉዳዮችን ለመከወን ምንም የሚቸግረን ነገር የለም፡፡ መሪ ሊያስፈልገን የሚችለው ከመንደሯ ከወጣን ብቻ ነው” ትላለች፡፡

ከፊሉ ዓይናማ ከፊሉ ዓይነ ስውር በሆነባት በዚህች መንደር ወንዱም ሴቱም ለኢስላማዊ ዕውቀት ያላቸው መሰጠት የሚያስደንቅ ነው፡፡

ሳቂታዋ ዓይነ ስውር ዓለም ላይ ቁርአን እንደማጥናት የሚያስደስታት ምንም ነገር እንደሌለ ትገልጸለች፡፡

የዳሊ ኩምቤው ኢማም ቡህ “ዓይንዎ ለአፍታ ቢበራ ምን ለማየት ይጓጓሉ?” ተብለው ሲጠየቁ መልሱን ለመስጠት ጥቂት ማሰብ አላሻቸውም፡፡

“ዓይኔ ለአፍታ ቢበራ ላየው የምመኘው ቁርአንን ነው፡፡ በአይምሮዬ ሸምድጄ የማስተምረውን የፈጣሪን ቃል በእጄ መጻፍ ካለመቻሌ በቀር አንዳች አልጎደለብኝም “ ይላሉ፡፡

ከ10 ትውልድ በፊት በህልም የተነገረው “ራዕይ“ አካል በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሚገልጹት ኢማሙ ፈጣሪ ያደረገላቸውን ለመዘርዘር አቅሙ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡

ኢማሙ ዓይን ማስተዋልን፣ መታዘዝን እና ትህትናን አጥፍቶ ፈጣሪን ወደ ማየት ካላደረሰ ለእርሳቸው ኪሳራ መሆኑን በአባትነት መክረው ሲያበቁ፣ “የቁርአን ማስተማሪያዬን ላሳይህ” ብለው የ‘ፕሮጀክት ሃፒነስ’ ጋዜጠኛውን እጅ ይዘው ወደ መድረሳ ቤታቸው መሩት፡፡

EBC

Send as a message
Share on my page
Share in the group