Translation is not possible.

ክፍል አንድ

የፆም ብይንን (ሑክምን) በተመለከተ

የረመዷንን ወር መፆም ግዴታነት በቁርአን፣ በሐዲስ እና በሙስሊሙ ማህበርሰብ ስምምነት (ኢጅማዕ) የተረጋገጠ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

[[ يَاأَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ (183) أَيَّامًا مَعْدُودَاتٍ فَمَنْ كَانَ مِنْكُمْ مَرِيضًا أَوْ عَلَى سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِنْ أَيَّامٍ أُخَرَ وَعَلَى الَّذِينَ يُطِيقُونَهُ فِدْيَةٌ طَعَامُ مِسْكِينٍ فَمَنْ تَطَوَّعَ خَيْرًا فَهُوَ خَيْرٌ لَهُ وَأَنْ تَصُومُوا خَيْرٌ لَكُمْ إِنْ كُنْتُمْ تَعْلَمُونَ (184) شَهْرُ رَمَضَانَ الَّذِي أُنْزِلَ فِيهِ الْقُرْآنُ هُدًى لِلنَّاسِ وَبَيِّنَاتٍ مِنَ الْهُدَى وَالْفُرْقَانِ فَمَنْ شَهِدَ مِنْكُمُ الشَّهْرَ فَلْيَصُمْهُ وَمَنْ كَانَ مَرِيضًا أَوْ عَلَى سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِنْ أَيَّامٍ أُخَرَ يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ وَلِتُكْمِلُوا الْعِدَّةَ وَلِتُكَبِّرُوا اللَّهَ عَلَى مَا هَدَاكُمْ وَلَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ ]] [البقرة: ١٨٣ - ١٨٥]

ትርጉሙም፦ «እናንተ ያመናችሁ ሆይ ፆም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነገገ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ የተቆጠሩን ቀኖች (ጹሙ)፤ ከናንተም ውሰጥ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነ ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መፆም አለበት፤ በነዚያም ፆምን በማይችሉት ላይ ቤዛ ድኻን ማብላት አለባቸው፤ (ቤዛን በመጨመር) መልካምንም ስራ የፈቀደ ሰው እርሱ (ፈቅዶ መጨመሩ) ለርሱ በላጭ ነው፤ መጾማችሁም ለናንተ የበለጠ ነው፤ የምታውቁ ብትኾኑ (ትመርጡታላችሁ)፡፡ (እንድትፆሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርአን የተወረደበት የረመዷን ወር ነው፤ ከናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፤ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መፆም አለበት አላህ በናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፤ በናንተም ችግሩን አይሻም፤ ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)፡፡» (አል-በቀራ፡ 183-185)

ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦ «ኢስላም በአምስት መሰረቶች ላይ ተገንብቷል:: እነርሱም፦ ከአላህ ሌላ አምልኮ የሚገባው አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ እንደሆኑ መመስከር፣ ሰላትን በተሟላ ሁኔታ መስገድ፣ ዘካን መስጠት፣ ወደተከበረው የአላህ ቤት ለሐጅ መጓዝ እና የረመዷንን ወር መፆም ናቸው::» (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

በሌላው የኢማሙ ሙስሊም ዘገባ «የረመዷንን ወር መፆም እና ወደ ተከበረው የአላህ ቤት ለሐጅ መጓዝ ናቸው::» በሚል (ቅደም ተከተል) ሰፍሯል።

የረመዷንን ወር መፆም ግዴታነት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአጠቃላይ ተስማምቶበታል:: ስለሆነም የረመዷንን ወር መፆም ግዴታነትን ያስተባበለ ከኢስላም በኋላ ወደ ክህደት የገባ (ሙርተድ) ተደርጎ ይቆጠራል:: ተውበት እንዲያደርግ ይመከራል ከዚህ አቋሙ ተመልሶ ግዴታነቱን ካረጋገጠ ይተዋል ካልሆነ ግን (በኢስላማዊ ህግ ስርአት በሚተዳደሩ ሀገሮች ውስጥ በህግ ፊት) ከሃዲ እንዳለ በሞት ይቀጣል::

የረመዷንን ወር መፆም ግዴታ የሆነው ከሂጅራ በሁለተኛው አመት ነበር:: በዚህም መሰረት መልእክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዘጠኝ ረመዷኖችን ፆመዋል:: ፆም በእያንዳንዱ ለአካለ መጠን በደረሰ እና ጤናማ አዕምሮ ባለው ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው:: ፆም ሙስሊም ባልሆነ (በካፊር) ላይ ግዴታ አይሆንም:: ኢስላምን እስካልተቀበለ ቢፆምም ተቀባይነት የለውም። ለአካለ መጠን እስካልደረሰም በሕፃን ልጅ ላይ ፆም ግዴታ አይሆንም። ወንድ ልጅ አስራ አምስት አመት በመሙላቱ ወይም በሀፈረተ-ገላው አካባቢ ያሉ ፀጉሮች በማደጋቸው አልያም በመኝታ ላይ እያለም ይሁን ከዚያ ውጪ የዘር ፈሳሽ ከፈሰሰው ለአካለ መጠን መድረሱ ሲታወቅ ሴት ልጅ ደግሞ ከነዚህ ምልክቶች አንዱን ወይም የወር አበባን በማየቷ ለአካለ መጠን መድረሷ ይታወቃል:: አንድ ታዳጊ ከነዚህ ምልክቶች መካከል አንዱ ከታየው ለአካለ መጠን ደርሷል ማለት ነው:: ሆኖም ታዳጊው ያለምንም መጎዳት መፆምን ከቻለ ለአካለ መጠን ባይደርስም ፆምን እንዲለምድ እና ለወደፊቱ የመፆም አቅምን እንዲያጎለብት በማሰብ እንዲፆም ይታዘዛል:: በአእምሮ መቃወስ አልያም በሌላ ምክንያት እራሱን በመሳቱ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች በትክክል ማሰብ የተሳነው ሰውም ፆም ግዴታ አይሆንበትም:: በዚህ መሰረት ነገሮችን መለየት የተሳነው የጃጀ ሽማግሌ የመፆምም ይሁን (ምስኪን) የማብላት ግዴታ የለበትም::

ኢንሻ አላህ ክፍል ሁለት ይቀጥላል…

ለሌሎች በማድረስ ለኢሰላማዊ እውቀት መስፋፋት የበኩላችንን አስተዋፅኦ በማበርከት የምንዳው ተቋዳሽ እንሁን።

አላህ ያግራልን!!

መንቁል!

Send as a message
Share on my page
Share in the group