Translation is not possible.

የረመዳን ገፀ በረከት

አንደኛው:- የፆመኛ የአፍ ሽታ ልክ እንደሚስክ ነው

አንድ ሰው ከምግብ ሲርቅ አፉ መጥፎ ጠረን ያመጣል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጠረን ሰዎች ዘንድ የተጠላ ቢሆንም አላህ ዘንድ ግን ከሚስክ ሽታ የተሻለ ጥሩ ሽታ ነው፡፡

ምክንያቱ ደግሞ አላህን በመታዘዝና በማምለክ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ማንኛውም አላህን በመተዘዝና በማምለክ የመጣ ነገር እሱ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው፡፡

አላህ ለሰራው ባለቤት የተሻለንና በላጭን ነገር ይተካዋል፡፡ ስለዚያ በአላህ መንገድ ላይ የአላህ ቃል የበላይ ትሆን ዘንድ ሲዋጋ ስለተገደለ ሰው ሰምተሃልን? የውመል ቂየማ ቁሱሉ ደም እያፈሰሰ ይመጣል፤ መልኩ ልክ እንደደም ነው ጠረኑ ደግሞ እንደሚስክ ነው፡፡

በሐጅ ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ አላህ መላኢኮችን አረፋ ላይ ስለቆሙ ሰዎች እንዲ ይላቸዋል “እነኝህን ባሮቼን ተመልከቱ፤ ፀጉራቸው ተንጨባሮና አቧራ ለብሰው ወደ እኔ መጡ፡፡”አህመድና ኢብኑ ሒባን ዘግበውታል

እዚህ ቦታ ላይ የፀጉር መንጨባረር አላህ ዘንድ ተወዷል፡፡ መነሻው አላህን መታዘዝና ኢህራምን ላለመፍታት እንዲሁም አለባበስን ከማሳመር መጠንቀቅ ስላለባት በመሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛው:መላኢካዎች እስከሚያፈጥሩ ድረስ ምህረትን ይጠይቁላቸዋል

መላኢካዎች አላህ ዘንደ የተከበሩ ካዘዛቸው ዝንፍ የማይሉ ከከለከላቸው የማይቀርቡ ብፁአን ፍጡር ናቸው፡፡ ለፆመኞች የሚያደርጉት ዱዓ በአላህ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ተቀባይነቱ ጥርጥር የለውም፡፡

አላህ ለዚህች ኡማህ መላኢካዎች ዱዓ እንዲያደርጉ መፍቀዱ የኡማዋን ትልቅነት፣ የዝናው ከፍ ማለትም የፆማቸውንም ታላቅ ትሩፋት ይገልፃል፡፡

ምህረት (ኢስቲግፋር) መፈለግ ማለት አንድ ሰው ወንጀል በዱንያ ሆነ በአኺራ ድብቅ እንዲሆንለት ይህችንም ወንጀል አላህ እንዲያልፈው መጠየቅ ማለት ሲሆን ይህ ደገሞ ከምንፈልጋቸውና ከምንመኛቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ በላጩ ነው፡፡ የአደም ልጆች ምንጊዜም ተሳሳቾችና ድንበር አላፊዎት ናቸው በመሆኑም የአላህን ምህረት መከጀል ይገባቸዋል፡፡

ሶስተኛ:-ሰይጣናት በሰንሰለትና እግረ ሙቅ ይታሰራሉ

እስራቱ መልካም የአላህ ባሪያዎችን እንዲያጠሙና ከሐቅ እንዳያዘናጋቸው ያደርጋል፡፡ ይህም የእሳት ባልደረቦች ይሆኑ ዘንድ ጥሪ የሚያደርጉ ጠላቶናቻቸውን በማገት አላህ ባሮችን የገዘበት መንገድ ነው፡፡

በዚህ ወር ላይ የሚታየው ከፍተኛ መልካም ስራን ለመፈፀም የሚደረግ ጉጉትና ከመጥፎ ነገር ለመታቀብ የሚደረገው ጥረት የሰይጣናቱ መታሰር ውጤት ነው፡፡

አራተኛው:-አላህ በየቀኑ ጀነትን ያስውባታል

ባሮቼ የሚያስከፋቸውንና የሚያስጠላቸውን ነገር እርግፍ አድርገው ትተው ወዳንቺ መምጣትን ፈልገዋል፣ ቀርበዋል ይላታል፡፡ አላህ ለመልካም ባሮቹ ለማዘጋጀት ያሰማምራታል በየቀኑ ባሮቹ ለእሷ ያላቸው ጉጉት ይጨምር ዘንድ፡፡

እንዲህም ይላታል ባሮቼ የዱንያ ጣጣን ትተው ሲያንገላታቸውና ሲያደክማቸው ሲያስቸግራቸው የነበረን ነገር ሁሉ በመተው በጐ ነገርን በመስራት ላይ ታጥቀው ተነስተዋል፡፡ ወደ ሰላሟና የክብረ ሀገሯ ጀነት የሚያደርሳቸው፣ የዱንያም የአኺራም ብቸኛ የደስታ ምንጭም ይህ መሆኑን አውቀዋል፡፡

አምስተኛው:-አላህ በዚህ በተባረከ ወር ሌሊቶች በተገቢው ሁኔታ ለሚቆሙ እና ለሚፆሙ ለነብዩ ሙሐመድ ሰዐወ ኡመቶች ምህረትን ይለግሳቸዋል

ይህም ሰዎች ስራቸውን በሚደመድሙበት ጊዜ የሚከፍላቸው ትሩፋት ነው፡፡ ሰራተኞች የስራ ዋጋቸው የሚከፈላቸው ሰራቸውን ሲያጠናቅቁ ነውና፡፡

አላህ ለባሮቹ በሶሰት መልኩ ችሮታውን ይለግሳቸዋል፡፡

አንደኛ

ኃጢአትን ለማሰማር ደረጃን ከፍ ለማድረግ የሚያስችልን መልካም ስራ ባሮች እንዲሰሩ መደንገጉ አንደኛው ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ባይኖር ኖሮ አላህን በዚህ መልኩ ማምለክ ባልቻሉ ነበር፡፡ ኢባዳ በራዕዩ መልክ ከአላህ ወደ መልዕክተኛው ሰዐወ የሚተላለፍ ነው፡፡

ለዚያም ነው ከአላህ ውጭ ሸሪዓን ወይም ስርዓተ ህግን የሚደነግጉ ሰዎችን ያወገዘውና የሽርክ ስራ እንደሆነ የገለፀው፡፡

“ከሃይማኖት አላህ በርሱ ያልፈቀደውን ለርሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለነርሱ አሏቸውን?”

ሁለተኛ

ብዙዎች ወደኃላ ያሉበትን መልካም ስራ እንዲሰሩ አላህ ገጠማቸው፡፡ የአላህ እርዳታና መገጠም ባይኖር ኖሮ ለዚህ ባልታደሉ ነበር ችሮታው የአላህ ነውና፡፡

“በመስለማቸው በአንተ ላይ ይመፃደቃሉ፤ በእስልምናችሁ በእኔ ላይ አትመፃደቁ፤ ይልቁንም አላህ ወደእምነት ስለመራችሁ ይመፃደቅባችኃል፤ እውነተኞች ብትሆኑ (መመፃደቅ ለአላህ ነው) በላቸው፡፡”

አል ሑጅራት 17

ሶስተኛ

አላህ ለኸይር ስራዎች ከፍተኛ ምንዳን አዘጋጅቷል፡፡ አንድ ሀሰና በአስር፣ በሰባት መቶ፣ በብዙ እጥፍ ድርብ ተባዝቶ ይሰጠዋል፡፡ ይህ ችሮታ የአላህ ነው፡፡ ምስጋና የተገባው ይሁን፡፡

ወንድሞቼ! የረመዷን መድረስ ትልቅ ፀጋ ነው ሐቁን መወጣት ለቻለና አላህን ከመወንጀል ትዕዛዛቱን ወደመፈፀም፤ ከዝንጋታ አላህን ወደ ማውሳት፤ ከአላህን መራቅ ወደ እሱ መመለስን ምርጫው ላደረገ ሰው እውነትም ታላቅ ፀጋ ነው፡፡

አንተ በረጅብ ወር ወንጀል ያልበቃህ

ከዚያም በሻዕባን የቀጠልህ

አሁን የፆም ወር መጥቶልሃል

እንደለመድከው

የኃጢአት ወር አታድርገው

ቁርአንን አንብብበት

ተስቢህም አድርግበት

ባለፈው የፆም ነበረ ስንትና ስንት

ከቤተሰብ ከወንድሞች ከጐረቤት

ግና ወሰዳቸው አይቀሬው ሞት

ለአንተ ጊዜ ሰጠህ እንድትማርበት

ጌታችን ሆይ ጠልቀን ከገባንበት ዝንጋታ አንቃን፣ ከሞታችን በፊት የተቅዋን ስንቅ ሰንቀን፣ ጊዜያችንን በከንቱ ከማባከን ጠብቀን፣ ለእኛም፣ ለወላጆቻችንም በጥቅሉ ለሁሉም ሙስሊሞች ምህረትን ለግሰን አንተ የአዛኞች አዛኝ ነህና፡፡

ምንጭ፦ መጃሊሱ ሸህሪ ረመዳን መፅሀፍዝፍጅት፦ ሸይኽ ሙሀመድ ቢን ሷሊህ አል ኡሰይሚንትርጉም፦ ያሲን አሊ

------------*********-------------

© ዝክረ ረመዳን አፕ ሸዕባን 2010

Ibnu Mas'oud Islamic Center

Send as a message
Share on my page
Share in the group