Translation is not possible.

ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት

የእነዚህን አሰርት የረመዳን ቀናት በተለይም ለሊቶችን ታላቅ ደረጃ የሚሰጣቸው ስለመሆኑ የተለያዩ ነጥቦችን ማንሳት ቢቻልም ዋና ዋናዎቹን ለመጠቆም፡

የረመዳን ወር ታላቅ ወር መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ስለታላቅነቱም ብዙ ሳንሰማ ወይም ሳናነብ አልቀረን ይሆናል፡፡ የረመዳን ወር የላቀ ታላቅ ወር እንደመሆኑ ሁሉ ከቀናቶቹና ከለሊቶቹ የመጨረሻዎቹ አስሩ ለየት ያለ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህን አሰርት የረመዳን ቀናት በተለይም ለሊቶች ታላቅ ደረጃ ልንሰጠቸው እንደሚገባ የሚያመለክቱ የተወሰኑ ነጥቦችን በአጭሩ ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡

አንደኛ፡- የአላህ መልዕክተኛ በነዚህ አስርት ቀናት እና ለሊቶች የነበራቸው የአምልኮ ሁኔታ የምዕመናን እናት ዓኢሻ (ረዲየላዑ ዓንሀ) እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹የአላህ መልዕክተኛ ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አስርት ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ (በዒባዳ) ላይ ይተጉ ነበር››

ሙስሊም ዘግበውታል

የአላህ መልዕክተኛው የለሊቱ አብዛኛውን ክፍል ከእንቅልፍ በመራቅ ህያው ያደርጉት ነበር፡፡ አሁንም ዓኢሻ (ረዲየላዑ ዓንሀ) እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹ የአላህ መልዕክተኛ ከረመዳን የመጨረሻዎቹ አሰርት ቀናት ሲገባ ለሊቱን በዒባዳ ላይ በማሳለፍ ህያው ያደርጉ፣ ቤተሰባቸውን ያነቃቁ (ይቀሰቅሱ) ፣ ቀበቷቸውን በማጥበቅ ይተጉ ነበር፡፡››

ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል

በሐዲሱ ውሰጥ ‹‹ቀበቷቸውን ያጠብቁ ነበር›› በሚል የተጠቀሰውን ቃል በተመለከተ ብዙ የሐዲስ ተንታኞች እንዳሉት ‘‘አሽሙራዊ አገላለፅ ሲሆን ለማለት የተፈለገውም በከፍተኛ ሁኔታ በዒባዳ ከመጠመዳቸው በመነሳት ከሴቶቻቸው ይርቁ ነበር ለማለት ነው’’ ፡፡

ሁለተኛ፡- የእነዚህን አሰርት ቀናት እና ለሊቶች ታላቅነት የሚያሳየን በውስጣቸው ‹‹ለይለተል ቀድር›› የተባለችው ለሊት መኖር ነው፡፡ ይህች ለሊት ከሌሎች የምትለይበት ብዙ መለያዎች ያላት ስትሆን ከነርሱም መካከል፡-

1.ቁርአን የወረደባት ለሊት መሆኗ

2.ከአንደ ሺህ ወራት የምትበልጥ መሆኗ

3.የተባረከች መሆኗ

4.ጅብሪል በመልዕክት በብዛት የሚወርዱባት መሆኗ

5.ሰዎች በከፍተኛ አምልኮ ውሰጥ የሚገቡ ከመሆኑ አንፃር ከእሳት ሰላም ወይም ነፃ የሚወጡባት ለሊት መሆኗ

5.ሰዎች በከፍተኛ አምልኮ ውሰጥ የሚገቡ ከመሆኑ አንፃር ከእሳት ሰላም ወይም ነፃ የሚወጡባት ለሊት መሆኗ

6.በዚህች ለሊት አላህ ምንዳውን እንደሚከፍለው በእርግጠኝነት በማመን እንዲሁም ከይዩልኝ እና መሰል ዱንያዊ ፍላጐቶች ርቆ ሰላትን መስገድ ያበዛ ወንጀሉ የሚታበስ መሆኑ ነው፡፡

ሶስተኛው፡- በእነዚህ አስር ቀናት ኢዕቲካፍ መግባት የመልዕክተኛው ሱና ነው፡፡ ኢዕቲካፍ ማለት እራስን ለአምልኮ ብቻ በመወሰን በመስጂድ መዘውተር ነው፡፡ እናታችን ዓኢሻ እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹ነብዩ እስኪሞቱ ድረስ ከረመዳን የመጨረሻዎቹን አስርት ቀናት እራሳቸውን ለአምልኮ ብቻ በመወሰን በመስጂድ ይዘወትሩ ነበር፡፡››

ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውተል

ከዚህ በመቀጠል ከኢዕቲካፍ ጋር ተያያዥነት ያለውን ይህንን ፈትዋ ወይም ጥያቄና መልስ እንመለከታለን፡፡

ጥያቄ፡- የኢዕቲካፍ መስፈርቶች የትኞቹ ናቸው? ፆም ከመስፈርቶቹ ይካተታልን? አንድ ሰው በኢዕቲካፍ ላይ እያለ በሽተኛን መጠየቅ፣ በግብዣ ቦታ ላይ መገኘት፣ የቤተሰቦቹን ጉዳይ ማስፈፀም፣ አስክሬን መሸኘት ወይም ወደ ስራው መሄድ ይችላልን?

መልስ፡- ሰላተል ጀመዓ በሚሰገድባቸው መስጂዶች ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ የተደነገገ ነው፡፡ ነገር ግን ኢዕቲካፍ የሚያደርገው ግለሰብ ሰላተል ጁምዓ ግዴታ ከሚሆንባቸው ሰዎች መካከል ከሆነና ከኢዕቲካፍ ቀናት መካከል የጁምዓ ቀን ካለ ሰላተልጁምዓ በሚሰገድበት መስጅድ ውስጥ ኢዕቲካፍን ማድረጉ የተሻለ (በላጭ) ነው፡፡

ፆም የኢዕቲካፍ መስፈርት አይደለም፡፡ እንዲሁም በኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው በዚያ ወቅት በሽተኛን አለመጠየቁ፣ ጥሪ ቢቀርብለት በጥሪ ቦታ ላይ አለመገኘቱ፣ የቤተሰቦቹን ጉዳዬች አለማስፈፀሙ፣ አስክሬን አለመሸኘቱ፣ ከመስጂድ ውጪ ወደ ስራው አለመሄዱ ሱና ነው፡፡ ይህም እናታች ዓኢሻ በትክክለኛ ሰነድ እንዲህ ማለታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ነው፡፡

‹‹በኢዕቲካፍ ላይ ያለ ሰው በሽተኛን አለመጠየቁ፣ የአስክሬን አሸኛኘት ላይ አለመገኘቱ፣ ግንኙነትን አለመፈፀሙም፣ በስሜት ከተቃራኒ ፆታ ጋር አለመተሻሸቱ፣ አስገዳጅ ለሆነ ጉዳይ ቢሆን እንጂ ከኢዕቲካፍ አለመውጣቱ ሱና ነው፡፡››

(አቡዳውድ እና ዳረቁጥኒ ዘግበውታል)

የሸይኽ ሙሀመድ ቢን ሳሊህ አል-ኡሰይሚን (ረሂመሁላህ) ስራዎችን መሰረት ያደረገዝግጅት፡- ኡስታዝ ጣሃ አህመድ

------------*********-------------

© ዝክረ ረመዳን አፕ ሸዕባን 2010

Ibnu Mas'oud Islamic Center

Send as a message
Share on my page
Share in the group