Translation is not possible.

ምስጋና ለሰው ልጆች ሁሉ በየዘመናቱ ወደ እርሱ ብቸኛ ተመላኪነት እንዲጣሩና በእርሱ ላይ ሌላን አካል ማጋራትን እንዲያስጠነቅቁ መልእክተኞችን ለላከው አምላክ አላህ ተገባው፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ በተወዳጁ ነብያችን በባልደረቦቻቸው እንዲሁም የእርሳቸውን ፈለግ በመልካም በተከተሉ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡

እንደሚታወቀው እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያውቀውና ሊገነዘበው ከሚገባ ወሳኝ ቁም ነገሮች መካከል ዋነኛው የተፈጠረበትን አላማ ነው። አላህ የሰው ልጆችን ፈጥሮ እንዲሁ በልቅ ለዛዛታና ጨዋታ አልተወም። ይልቁኑ ለታላቅ አላማና ግብ በየጊዜው መልዕክተኞችን እየላከ ወደ ተፈጠሩበት እርሱን በብቸኝነት ማምለክ ተውሒድ ይጠራ ፣ በአምልኮ ላይ በእርሱ ላይ ሌላን ከማጋራት ሽርክ ያስጠነቅቅ ነበር። ከመጀመሪያው ረሱል ኑሕ ጀምሮ እስከ ነብያት መደምደሚያና የሰው ልጆች አለቃ የሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ (ﷺ) ድረስ ሁሉም ነቢያት አንግበው የተላኩት ዋና አላማ ይህ ነበር፡፡

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِى كُلِّ أُمَّةٍۢ رَّسُولًا أَنِ ٱعْبُدُوا۟ ٱللَّهَ وَٱجْتَنِبُوا۟ ٱلطَّـٰغُوتَ “በየህዝቡም ሁሉ ዉስጥ አላህን አምልኩ ጣዖታትንም ራቁ በማለት መልዕክተኞችን በእርግጥ ልከናል (ነሕል :36)

ተወዳጁ አርዓያችንና ነብያችን (ﷺ) ወደ ተውሒድ ለ23 አመታት ተጣሩ። በተለይም ደግሞ በመጀመሪያዎቹ የነብይነት 10 አመታት በዋነኝነት እርሱን ሰበኩ። አላህ ብቻ ተነጥሎ እንዲመለክ ጣሩ፤ በዚህም ሳቢያ በመካ ላይ ግፍና በደሉ ሲያይል ወደ መዲና ተሰደዱ። በዚያም ቆይታቸው ተውሒድንና ሌሎች የእስልምና ድንጋጌዎችን አስተማሩ።

ሶሐቦቻቸውን ለዳዕዋ ሲልኩ የሚያስጨብጧቸው ቀዳሚና ዋነኛው ተልዕኮ ተውሒድ ነበር። ኢብኑ አባስ እንዳወሩት ነቢዩ (ﷺ) ሙዐዝን ወደ የመን በላኩት ግዜ እንዲህ አሉት፦

“አንተ የምትሄድባቸው ሰዎች የመጽሀፍ ባለቤቶች ናቸው። መጀመሪያ የምትጠራቸው ወደ “ላኢላሀ ኢለላህ” (ከአላህ ውጪ በእውነት የሚገዙት አምላክ እንደሌለ) መመስከር ይሁን። ይህን ከተቀበሉክ አላህ አምስት ወቅት ሶላት ግዴታ እንዳደረገባቸው አሳውቃቸው……”[አል ቡኻሪይ (1497) ፣ሙስሊም (19) ፣ አቡ ዳውድ (1587) ፣ቲርሚዚይ (625) ፣ነሳኢይ (2434) ፣ኢብኑ ማጃህ (1783) ፣አሕመድ (1/233) ዘግበውታል።]

አንገብጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለዐቂዳ ነው። ምክንያቱም የአንድ ሰው እስልምና መሰረቱ ዐቂዳ ስለሆነ ነው። ዐቂዳው ወይም እምነቱ የተስተካከለ ሰው መላ ስራው ይስተካከላል። መሰረቱ ከተበላሸ ግን ግንቡ ያምራል ተብሎ አይጠበቅም። የሰራውም ስራ ከሽርክ ጋር ከተነካካ ዋጋ የለውም። አላህ በተከበረ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

وَلَقَدْ أُوحِىَ إِلَيْكَ وَإِلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِكَ لَئِنْ أَشْرَكْتَ لَيَحْبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ ٱلْخَـٰسِرِينَ“ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፡፡ በእርግጥም ከከሳሪዎች ትሆናለህ በማለት ወደ አንተም ወደ እነዚያም ካንተ በፊት ወደ ነበሩት በእርግጥ ተወርዷል፡፡”(ዙመር:65)

------------*********-------------

ሐይደር ኸድር ዐብደላህ (አቡ ሐማድ)

ረጀብ 13/ 1438

ሚያዝያ 2/ 2009

haiderr02@gmail.com

Send as a message
Share on my page
Share in the group