Translation is not possible.

ፆምን የማያበላሹ ነገሮች

1. አንድ ሰው ፆመኛ መሆኑን ረስቶ ወይም ተገዶ ወይም ፆም የሚያበላሽ መሆኑን ስለማያውቅ ፆም የሚያፈርስ ነገር ከፈፀመ(ቢበላ፣ቢጠጣ…) ፆሙ አይበላሽም፡፡ ይህም ቀጥሎ በተመለከተው የአላህ ቃል መሰረት ነው፡-

‹‹(በሉ)፡- ጌታችን ሆይ! ብንረሳ ወይም ብንስት አትያዘን (አትቅጣን)››

(2፡286)

‹‹ልብ በእምነት የረካ ሆኖ(በክህደት በመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር፤…››

(16፡ 106)

‹‹በርሱ በተሳሳታችሁበት ነገርም በናንተ ላይ ኃጢያት የለባችሁም ነገርግን ልቦቻችሁ አውቀው በሰሩት ኃጢያት አለባችሁ››

(33፡5)

2.ጾመኛ ሰው ረስቶ ቢበላ ወይም ቢጠጣ ሳያውቅ ዘንግቶ ነውና ጾሙ አይበላሽም፡፡

3.ጸሐይ የጠለቀች መስሎት ወይም ጎህ ያልቀደደ መስሎት ቢበላ ወይም ቢጠጣም ሳያውቅ ነውና ጾሙ አይበላሽም፡፡

4.ሲግሞጠሞጥ ውሀ ከጉሮሮው ቢደርስ ሆን ብሎ ፍልጎ እና በእቅድ እስካላደረገ ድረስ ፆሙ አይበላሽም፡፡

5. በሕልሙ ሩካቤ ስጋ ቢፈፅም በራሱ ምርጫ አይደለም እና ፆሙ አይበላሽም፡፡

ፆም የሚያበላሹ ነገሮች ስምንት ናቸው

1.ሩካቤ ስጋ፡- አንድ የፆም ግዴታ የሚፀናበት ፆመኛ በረመዷን ቀን ወሲባዊ ተራክቦ ከፈጸመ ጾሙን ጹሞ ከመክፈል ጋር ከፍተኛው የመካካሻ ክፍያ(ኩፍፋራ) ይጸናበታል፡፡ ከፍፋራውም አንድን የጫንቃ ተገዥ(ባሪያ) ነጻ ማውጣት ሲሆን ካልተገኘ ሁለት ተከታታይ ወራት መጾም ነው፡፡ ጾሙን ካልቻለ ደግሞ 60 ድሆችን (ሚስኪኖችን) መመገብ ነው፡፡

2.የዘር ፈሳሽ ከእንቅልፍ ውጭ ብልትን በመነካካት ከተቃራኒ ጾታ ጋር በመተሻሸት በመተቃቀፍ በመሳሳምና በመሳሰሉት መንገዶች መፍሰስ፡፡

3.ጠቃሚም ይሁን ጎጂ ነገር እንደ ሲጋራ ያለ ቢሆንም መብላትና መጠጣት ጾም ያስፈታል፡፡

4.በምግብ ፋንታ ሊያገለግል የሚችል የሕክምና መርፌ መወጋት ጾም ያበላሻል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መርፌ ቀለብ ሆኖ ምግብና መጠጥን መተካት ይችላል፡፡ የምግብነት ባህሪ የሌላቸው የህክምና መርፌዎች በጡንቻዎችም ሆኑ በጅማቶች በኩል ቢወሰዱ ጣዕሙ አፉ ውስጥ ቢሰማውም ባይሰማውም ጾም አይበላሽም፡፡

5.ጾመኛው ለምሳሌ ብዙ ደም ፈሶት ሌላ ደም እንዲሰጠው ካስፈለገ ይህም ጾሙን ያበላሻል፡፡

6.የወር አበባ እና የወሊድ ደም መምጣትም ፆም ያፈርሳል፡፡

7.ደምን በዋግምት እና በመሳሰሉት ከሰውነት ሆን ብሎ እንዲወጣ ማድረግ ፆም ያበላሻል፡፡ ሆን ተብሎ ሳይሆን እንደ ነስር እና ጥርስ ነቀላ በመሳሰሉት ምክንያቶች እንዲሁ የሚወጣ ከሆነ ግን ፆም አይበላሽም፡፡

8.ሆን ብሎ ፈልጎ ማስታወክም ፆም ያበላሻል፡፡ ያለፍላጎት ካስታወከው ግን ፆም አያበላሽም፡፡

የሸይኽ ሙሀመድ ቢን ሳሊህ አል-ኡሰይሚን (ረሂመሁላህ) ስራዎችን መሰረት ያደረገ

------------*********-------------

© ዝክረ ረመዳን አፕ ሸዕባን 2010

Ibnu Mas'oud Islamic Center

Send as a message
Share on my page
Share in the group