Translation is not possible.

የሸይኽ ሙሀመድ ኢብኑ አብዱልዋሀብ ትክክለኛው አቂዳ

✍ክፍል 1

~~

ሸይኽ ሙሀመድ ኢብኑ አብዱልዋሀብ ለተውሂድ የታገሉ ብዙ መስዋእትነትን የከፈሉ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ሱናን ያሸተተ ወደ ታሪካቸው መለስ ብሎ የተመለከተ ሁላ የሚረዳው እውነታ ነው።

ሸይኽ ሙሀመድ ኢብኑ አብዱልዋሀብ በተውሂድ ዙርያ የፃፏቸው መፅሀፍቶች ለስንቱ ቅናቻ ምክንያት ለብዙዎች ፅናት መሰረት የሆኑ ዘመን ተሻጋሪም ጭምር ናቸው።ስለ ሸይኹ ታላቅነት ምንነት የሸይኹ ዳእዋ መሰረት ብዙ መፅሀፍቶች ከብዙ ከሳቸው በኋላ ከመጡ ትላልቅ የዲን ሊቃውንቶች ባለ ብዙ ጥራዝ ባለብዙ ገፆች መፅፍቶች ተፅፈዋል። በተቃራኒው በግዜያችን እንዲሁም በግዜያቸውም ጭምር በእሳቸው ላይ ብዙ ቅጥፈቶች መሰረተ ቢስ ልብወለዶች ሲነዙ ሲፈበረኩ ቆይተዋል። ሸይኹም በተቻላቸው አቅም ያሉበትን የያዙት እውነተኛ አቂዳ ለግለሰብ ለጀመአም በድምፅም በደብዳቤ ፅሁፍም ገልፀዋል። አቂዳቸውን ከገለፁበት ደብዳቤዎቻቸው ውስጥ ለቀሲም ሰዎች ስለ አቂዳቸው በተጠየቁ ሰአት የፃፉትን ደብዳቤ በተወሰነ መልኩ እንመልከት። ምንምንኳ ሸይኹ የፃፉት ደብዳቤ በርዕስ የተከፉፈለ ባይሆንም ለአንባንቢ ውስብስብና አሰልቺ እንዳይሆን በመስጋት ርእሶችን አብጅቼላቸዋለሁ። በተጨማሪም ሸይኹ የተጠቀሷቸውን ቡድኖች ምንነት ከተለያዩ የአቂዳ ድርሳናት ማብራሪያ በመቀነጫጨብ በአጭሩ ለማብራራት ሞክሬያለሁ።

ከሁሉ በፊት ግን ስለ ሸይኹም ሆነ ስለተቀሩት የዲን ሊቃውንቶች አሉባልታን በማመን ጥላቻን ከማራመዳችን በፊት ስለሸይኹ ማንነት ስለተፃፉ እውነተኛና እውነታውን ስለሚያስረዱ ኪታቦች ራሳቸውም ሸይኹ ስለፃፏቸው ኪታቦች መለስ ብለን ሀቁን ማጥናታችን ከብዙ ይቅር ሊባሉ ከማይችሉ ስህተቶች እንድናለን። ይህ ወንድማዊ ምክሬ ነው በተረፈ መልካም ንባብ።

➥*ሸይኽ ሙሀመድ ኢብኑ አብዱልዋሀብ በአላህ ስሞችና መገለጫዎች ያላቸው አቋም

~

ሸይኹ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ይላሉ“ አላህ (ስራዬን በመመዝገብ) የተጣዱ መላእኮችና እናንተም ምስክሮቼ ናችሁ። እኔ የምትድነዋ ቡድን አህለልሱና ወልጀማአዎች ከአላህ ከመልአኮቹ ከመፅሀፍቱ ከመልእክተኞቹ ከሞት በኋላ መቀስቀስ እንዳለ መልካምም ይሁን መጥፎ ከአላህ ውሳኔዎች የሚያምኑትን ሁሉ አምናለሁ። በአላህ ከማመን ውስጥ አላህ በመፅሀፍቱ ውስጥና በመልእተኛው ﷺ አንደበት ራሱን በገለፀባቸው መገለጫዎች ሁሉ ያለምንም ማራቆት ማዛባት ማመሳሰልና ዝርዝር ሁኔታቸውን ያለማስቀመጥ አምናለሁ። ይልቁንስ እሱን የሚመስል ፍፁም እንደሌለ እርሱም ሰሚና ተመልካች እንደሆነ አምናለሁ። አላህ ራሱን የገለፀባቸውን ውድቅ አላደርግም ቃላቶችን ከመቀመጫቸው አላጣምም ከአናቅፆቹና ከስያሜዎቹ አንድንም አላዛባም።(ለባህርያቱም) ዝርዝር ሁኔታን አላስቀምጥም። የፈጣሪን መገለጫ ባህሪ ከፍጡር መገለጫ ባህርያቶች ጋር አላመሳስልም። ምክንያቱም አላህ አምሳያ ብጤና ባላንጣ የለውም በፍጥረታቱም አይለካም። እሱ አላህ ስለራሱም ይሁን ስሌሎች ይበልጥ አዋቂ እውነትን ምርጥን ንግግር ተናጋሪ ነው።

አላህ (ከቀጥተኛው መንገድ) የተቃረኑ የሆኑ የተክዪፍና የተምሲል ሰዎች እሱን ከገለፁበት ነገር እንደዚሁም ውድቅ አድራጊያን የተእጢልና የተህሪፍ ሰዎች ከሱ ውድቅ ከሚያደርጉት ነገር ሁሉ ራሱን አጠራ። እንዲህ አለ አላህ

سُبۡحَٰنَ رَبِّكَ رَبِّ ٱلۡعِزَّةِ عَمَّا يَصِفُونَ ١٨٠۞وَسَلَٰمٌ عَلَى ٱلۡمُرۡسَلِينَ ١٨١۞وَٱلۡحَمۡدُ لِلَّهِ رَبِّ ٱلۡعَٰلَمِينَ ١٨٢

ጌታህ-የአሸናፊነት ጌታ-ከሚገልፁት ሁሉ ጥራት የተገባው ነው! ۞በመልእክተኞቹም ላይ ሰላም ይሁን۞ ምስጋናም ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ ይሁን۞[አስ-ሷፍፋት: 180-182]»

ይቀጥላል...

✍️Abdulkerim husen (Abu suleyman

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group