👉 የሴትና የዱንያ ፊትና
ክፍል አንድ
የአላህ መልእክተኛ – ሶለላሁ ዓለይሂ ወሰለም – ሁለት አጥፊ ነገሮችን እንድንጠነቀቅ እንዲህ ብለው መክረውናል : –
عن أبي سعيد الخدري – رضي الله عنه – قال : قال رسول الله – صلى الله عليه وسلم –
" إنَّ الدُّنْيَا حُلْوَةٌ خَضِرَةٌ، وإنَّ اللَّهَ مُسْتَخْلِفُكُمْ فِيهَا، فَيَنْظُرُ كيفَ تَعْمَلُونَ، فَاتَّقُوا الدُّنْيَا وَاتَّقُوا النِّسَاءَ؛ فإنَّ أَوَّلَ فِتْنَةِ بَنِي إِسْرَائِيلَ كَانَتْ في النِّسَاءِ. وفي روايةٍ: لِيَنْظُرَ كيفَ تَعْمَلُونَ ".
رواه مسلم
🔹 አቡ ሰዒድ አል ኹድርይ የተባለ ሶሐብይ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል ይላል: –
" ዱንያ ( ሲበሉት) ጣፋጭና ( ሲያዩት ) አረንጓዴ ነው ። አላህ በሷ ( በዱንያ ) ላይ ምትክ አድራጊያችሁ ነው ። እንዴት እንደምትሰሩ ያያል ። ( በሌላ ዘገባ እንዴት እንደምትሰሩ ሊያይ ተብሏል ) ። ዱንያን ተጠንቀቁ ሴቶችንም ተጠንቀቁ ። የኢስራኢላዊያን የመጀመሪያ ፈተና በሴቶች ነበር ።
በዚህ ነብያዊ ምክር የአላህ መልእክተኛ ከዱንያና ከሴቶች እንድንጠነቀቅ መክረውናል ። የአላህ መልእክተኛ ከዛሬ 1400 አመት በፊት የተናገሩት ንግግር ዛሬ ያለውን ሁኔታ ላየ ለዚህ ተውልድ ብቻ ነው ይል ነበር ።
ከእነዚህ ሁለት ፈተናዎች ለዛሬ አንዱን እንመልከት ።
➡️ የሴቶችን ፈተና : –
የሴቶች ፈተና ሲባል ብዙ ጊዜ ተራቁተው የሚሄዱ ሴቶች የወንዶችን ደመነፍሳዊ ስሜት በመቀስቀስ የሚያመጡትን ፈተና ነው በሰዎች ልቦና ላይ ውል የሚለው ። ነገር ግን የሴቶች ፈተና ሲባል አድማሱ በጣም ሰፊ አይነቱም ብዙ ነው ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን ለማየት ያክል የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት : –
– የሚስት ፈተና
ከሴት ፈተና ውስጥ ትልቁ ሚና የሚጫወተው የሚስት ፈተና ነው ። ሚስት አላህን የማትፈራ ከሆነች በባልዋ ላይ በብዙ መልኩ ፈተና ትሆናለች ። ከእነዚህ ውስጥ : –
– ትእዛዙን አለመቀበል
ራስዋን ከሱ እኩል ባለመብት በማድረግ ሌላው ቀርቶ ሶላት እንኳን ስገጂ ሲላት አሻፈረኝ ትላለች ።
– ሐዘን ቢኖር ፈተና ናት ።
– ሰርግ ቢኖር ፈተና ነ ።
– መጣለት ቢኖር ፈተና ናት።
–በንብረት ላይ ባለት አቋም ፈተና ናት ።
– የሱን ቤተሰቦች በማግለል ፈተና ናት ።
– የልጆቿን ስብእና በማበላሸት ፈተና ናት ።
– ክብሯን በማስደፈር ፈተና ናት ።
– ወሬ በማመላለስ ፈተና ናት ።
– የሌላውን ኑሮ እያየች እቤት ውስጥ ሚጥሚጣ በመሆን ፈተና ናት ። ፈተናዋ ተቆጥሮ አያልቅም ። አላህን የምትፈራ ከሆነች በተቃራኒው የደስታና እርካታ ቁልፍ ናት ።
– የልጅ ፈተና
አላህን የማትፈራ ሴት ልጅም ፈተና ናት ። ሴት ልጅ አላህን የማትፈራ ከሆነች አላህ የከለከለውን ተግባር በመፈፀም በወላጅዋ ላይ ፈተና ናት ። በአለባበስዋ ፣ በአዋዋልዋ ፣ በአወጣጥዋ ፣ በአገባብዋ ፣ በጓደኛ አያያዝዋ ፣ በየአንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ፈተና ናት ።
– የአጅ ነብይ ( ከባዳ ሴት ጋር ) የመቀራረብ ፈተና
ይሄኛው ፈተና በተለይ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈሪ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው ። በየመንገዱ የሚታየው ፈተና ትተን ዲን አለን ብለው ለዛው ወደ ሱና እንጣራለን በሚሉ ወንድምና እህቶች የባሰ ይመስላል ።
እንደሚታወቀው ኢስላም አንድን ነገር ሲከለክል ወደዛ ክልክል የሚያዳርሱ ነገሮችንም ክልክል አድርጓል ። ዝሙትን ሲከለክል ወደ ዝሙት የሚያዳርሱ መንገዶችንም ክልክል አድርጓል ።
ከነዚህ ውስጥ ለሸሪዓዊ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር መተያየትን ፣ መሕረም ያለሆነችን ሴት መጨበጥን ፣ ማንም ሰው ቢሰማው ችግር የሌለው አይነት ንግግር ካልሆ በስተቀር መነጋገርን ፣ ድምፅ ማቅለስለስን ፣ ሁለት ሆኖ አንድ ክፍል ላይ መሆንን ወይም ከወንድ ጋር መቀላቀልንና የመሳሰሉትን ከልክሏል ።
ይህ ከመሆኑ ጋር በኡኑ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት እነዚህ ሁሉ ክልከላዎች ተጥሰው እናገኛለን ።
ግሩፕ ይከፈታል ወንድና ሴት ይደበላለቃል ። በዚህ አያበቃም አንድ የሱና ኡስታዝ የተባለን ኡስታዝ በውስጥ መስመር ገብታ ሴቷ ታነጋግረዋለች ‼ ። መጀመሪያ ጥያቄ ነበረኝ ተብሎ ይጀመራል ። ይቀጥላል ምከረኝ ይመጣል ። ምክር ይጀመራል ። ይቀጥላል ድምፅ መነፋፈቅ ይከተላል እየተባለ ወደ ቀይ መስመር ይገባል ።
በዚህን ጊዜ ሁሉ ኸልዋ ተገኝቷል ማለት ነው ። ምክንያቱም ሁለቱ ከግሩፑ ተነጥለው ወጥተው ዐለመል ጂኒ ውስጥ ባለ ክፍል ውስጥ ሆነው ነው የሚያወሩትና ። በዚህ ጊዜ ምናልባትም ኡስታዙ ሚስትና ልጅ ያለው ይሆናል በዚህም ምክንያት ትዳሩ ሊፈርስ ይችላል ። በሴትዋም በኩል እንደዚሁ ።
የሚገርመው በዚህ መልኩ ያገኘችውን ወይም ያገኛትን በዛኑ መንገድ ሌላ ሊወስደውና ይሄኛውንም ትዳር ሊያፈርሰው ይችላል ብለው ሳያስቡ ትዳር ብለው መግባታቸው ነው ። መጨረሻው በሰፈሩበት ቁና መሰፈር ነውና የሚሆነው ።
ምናልባትም ወደ ትዳር ሳይደርስ በተለይ ኡስታዝ ተብዬው ወይም ዲን አለው የተባለው ጎረምሳ የሷን ላብ አሟጦ የሌሎችንም በርሷ አማካይነት በዲን ስም ሰብስቦ በዛው ሊጠፋ ይችላል ። ይሄኛው በብዛት የሚከሰት ነው ።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ሸሪዓ ከላይ እንዳስቀመጥነው በአጅ ነብዮች መካከል ለሸሪዓዊ ምክንያት ካልሆ በስተቀር መቀራረብን ከልክሎ ሳለ ነው ። ይህ ክልክል የሁለት አጅ ነብዮች ለሸሪዓዊ ምክንያት ካልሆ በስተቀር ስልክ ሴቭ መደራረግን ጭምር ይከለክላል ።
ይህን አይተን ዛሬ ዱዓቶችና ኡስታዞች ከሚባሉት አብዛኞቹ ያሉበትን ብንመለከት ምን ያክል ከሸሪዓ መራቅ እንዳለ እናያለን ።
– የሴቶች ፊትና መድረሳዎች አካባቢ :–
መድረሳዎች አካባቢ ያለው የሴቶች ፊትና የሰለፍዮችን ጀማዓ እስከማፍረስና እስከመበታተን ይደርሳል ። ይህም የሚሆነው ሴቶቹ በኮሚቴዎች መካከል ወሬ በማመላለስና የቤት ውስጥ ችግርን ወደ ጀማዓ በማውጣት ሊሆን ይችላል ። ሌላኛው መድረሳ አካባቢ ባሉ ወንድሞችና ሴቶች መካከል ክልክል የሆኑ ነገሮች ባለመጠንቀቅ በሚደረግ መቀራረብ ይሆናል ። ከዚህም ሲያልፍ ኡስታዙ ከተወሰኑ ሴቶች ጋር በሚኖረው ሸሪዓን የጣሰ መቀራረብ ሊሆን ይችላል ። ከተማሪዎቹ ውስጥ የተወሰኑትን ስልካቸውን በመያዝ በግል ደውሎ በማዋራትና የመሳሰሉት መንገዶች ።‼
እነዚህ እንደምሳሌ ማሳያዎች እንጂ መሬት ላይ ያለው ጉድ ከዚህ በጣም የከፋ ነው የራስንም የዲንንም ክብር ለመጠበቅ መጠንቀቁ ይበጃል ።