Translation is not possible.

የዲሞክራሲ አንድ ሽንቁር

~

ዲሞክራሲ ብዙ ሽንቁሮች አሉት፡፡ በነዚህ ሽንቁሮቹ የተነሳ አፍቃሪዎቹ ሳይቀሩ የሰላ ሂስ ሲሰነዝሩበት ይታያል፡፡ ከነዚህ ሽንቁሮች ውስጥ አንዱ ዜጎች ለምርጫ ብቁ የሚሆኑበት ስርኣቱ ነው፡፡ በትልልቅ ሀገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ

1. የመሀይማን ድምፅ ከምሁራን፣

2. የዋልጌዎች ከጨዋዎች፣

3. የጠርዘኞች ከአስተዋዮች፣

4. የጠባብ ብሄርተኞች ሁሉን አቀፍ ራእይ ካላቸው፣

5. አፍላ እድሜ ላይ ያሉ ጎረምሶች ድምፅ እድሜ ካስተማራቸው ጎልማሶችና ሽማግሌዎች ድምፅ ጋር እኩል ይቆጠራል፡፡

ይሄ እጅግ አደገኛ ውጤት የሚያስከትል ቀዳዳ ነው፡፡ በትልልቅ ሃገራዊ ጉዳዮችና ፖሊሲዎች ላይ እንዴት ምሁር ከመሀይም እኩል የመወሰን እድል ይሰጠዋል?! አገርንና ወገንን የሚጎዳ አደገኛ ውሳኔ እንዳይወሰንስ ምን ዋስትና አለ? ይሄ እጅግ በጣም የሚደንቅ ነገር ነው፡፡

ይሄ እንግዲህ በመራጭ በኩል ያለውን የሚመለከት ነው፡፡

ተመራጮችን በተመለከተም አንድ ቤቱን እንኳን ማስተዳደር ያቃተው የመንደር ዱርየ እንደ ዋዛ የአንድ ፓርቲ ተወካይ ሆኖ “የምረጡኝ” ቅስቀሳ ሲያደርግ ማየት በብዛት የተለመደ ነው፡፡ ከህዝባችን ውስጥ ደግሞ ከምሁራን ይልቅ መሀይማኑ፣ ከጨዋው ይልቅ ዋልጌው፣ ከአስተዋዩ ይልቅ ጠርዘኛው፣ ሁሉን አቀፍ ራእይ ካለው ይልቅ ጠባብ ብሄርተኛው፣ እድሜ ካስተማረው በሳል ይልቅ ጎረምሳው ይበዛልና ከምላስ አክሮባት የዘለለ ይሄ ነው የሚባል ስክነትና ብስለት የሌለው የመንደር ወጠጤ ሁሉ በሃገራዊ ጉዳይ ላይ እንደዋዛ ሲመረጥ ያጋጥማል፡፡ ከመራጭም ከተመራጭም በኩል ያሉ የአስተሳሰብ እንጭጮች ተደማምረው ሃገርን ያክል ነገር ወደ ገደል የመውሰድ እድል በቀላል ያገኛሉ፡፡

በእንደዚህ አይነት ከባባድ የዲሞክራሲ ሽንቁሮች እያለፉ ነው እንደ ግብረ ሰዶማዊነት ያሉ የህዝብን ሞራል የሚያላሽቁ የስነ ምግባር ዝቅጠቶች በምእራቡ አለም በሰፊው እየፀደቁ ያሉት፡፡ በእንደዚህ አይነት ቀዳዳዎች ሰበብ ነው ክልሎች እየተገነጠሉ ሃገራት የሚሸራረፉት፡፡ ለጠጋኝ ያታከተ የዲሞክራሲ ሽንቁር!

Send as a message
Share on my page
Share in the group