(أليس فيكم ابن أم الدهماء؟! يقصد سعيد بن جبير.)
"በመካከላችሁ ኢብኑ ኡሚ ደህማእ የለም እንደ?!"
(ኢብኑ ኡሚ ደህማእ ማለት ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ነው።) እንግዲህ አስቡት ምን ያክል ታላቅ ሰው እንደነበር!!
✔️ ወደ ታላቁ ሶሐባ ዐብደል'ሏህ ኢብኑ ዑመር ዘንድ አንድ ሰው መጣና ስለ ውርስ ጠየቃቸው። እርሳቸውም "ወደ ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ዘንድ ሂድ!፤ እርሱ ከኔ ይበልጥ በሒሳብ ረገድ አዋቂ ነው!" አሉት።
✔️ ኢብራሂም አን-ነኸዒይ እንዲህ ይላሉ፦ "ከሰዒድ ኢብኑ ጁበይር በኋላ የርሱ አምሳያ አልተተካም።"
✔️ አሽዓት ኢብኑ ኢስሐቅ እንዲህ ይላሉ፦ "ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር የዑለማዎች ፈርጥ ነው።"
✔️ አቡ ቃሲም አል-ላለካኢይ እንዲህ ይላሉ፦ "እርሱ (ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር) ታማኝ ነው። በሙስሊሞች ላይ ማስረጃ የሚሆን ሰው ነው።"
✔️ ዐልይ አል-መዲኒይ እንዲህ ይላሉ፦
(ليس في أصحاب ابن عباس مثل سعيد بن جبير، قيل: ولا طاوس؟ قال: ولا طاوس، ولا أحد)
"ከኢብኑ ዐብ-ባስ ባልደረቦች (ተማሪዎች) ውስጥ እንደ ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ያለ አምሳያ የለም።
'ጧውስም ቢሆን?" ተባሉ። "አዎ! ጧውስም ቢሆን!!" አሉ። ሌሎችም ቢሆኑ።"
✔️ መይሙን ኢብኑ ሚህራን እንዲህ ይላሉ፦ "ወደ እውቀቱ የፈለገ ቢሆን እንጂ፤ በምድር ላይ የማይወጣ ሁኖ ሳለ ሰዒድ በርግጥ ሞተ።"
✔️ ከኢብኑ ዐብ-ባስ ባልደረቦች ውስጥ አንዱ የሆኑት ኸዺፍ ኢብኑ ዐብዱር-ረ-ሕማን እንዲህ ይላሉ፦
(كان أعلمهم بالقرآن مجاهد، وأعلمهم بالحج عطاء، وأعلمهم بالحلال والحرام طاوس، وأعلمهم بالطلاق سعيد بن المسيب، وأجمعهم لهذه العلوم سعيد بن جبير.)
"(ከታቢዒዮች) ከመካከላቸው በቁርኣን ይበልጥ አዋቂያቸው ሙጃሂድ ነበር። ስለ ሐጅ ደግሞ ይበልጥ አዋቂያቸው ዐጧእ ነው። ስለ ሐራምና ሐላል (ክልክልና ፍቁድ ነገራቶች) ይበልጥ አዋቂያቸው ጧውስ ነው። ስለ ፍች ይበልጥ አዋቂያቸው ሰዒድ ኢብኑ ሙሰየብ ነው። እነዚህን የእውቀት ዘርፎች በሙሉ አካቶ ይበልጥ አዋቂያቸው ደግሞ ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ነው።"
አስባችሁታል?! ሰኢድ ምን ያክል ዐሊም እንደሆነ!!
||
♠ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ከዒልሙ ባሻገር ይበልጥ አላህን ፈሪ፣ በርሱም ላይ ተመኪ፣ እጅጉን ተናናሽ ነበር።
ከእለታት አንድ ቀን ሌሊት ላይ እየሰገደ ሳለ ሲያለቅስ፤ ያለቀሰበት አይኑ ሲነጋ እይታዋ ደከመ። ሐጂና ዑምራ በየ አመቱ ያደርግ ነበር። ቁርኣን በሶስት ቀን ውስጥ ያኸትም ነበር። በአንዳንድ ዘገባዎች ላይ እንደሰፈረው እንዳውም በአንድ ቀን ያኸትም ነበር ይላል። ብቻውን ሲሰግድ ለማኽተም ብሎ መቆሙን ይበልጥ ያስረዝም ነበር።
♠የሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ታሪክ ይህን ይመስላል።
ከዚህ ታሪክ ብዙ የምንማራቸው ቁም ነገሮች አሉ።
①, የሰዒድ ኢብኑ ጁበይርን ታላቅነትና የታላላቅ ታቢዒዮችን ውዳሴ።
②, የሰዒድ ዱዓ ተቀባይነት። ሐጃጅ እርሱን ከገደለ በኋላ በህይወት ብዙም ቀን አልቆዬም። በአንዳንድ ዘገባዎች ላይ እንደሰፈረው አርባ ቀን ሲሆን በአንዳንዶች ላይ ደግሞ ሃምሳ ቀን ነው፤ እነዚሁንም በከባድ ስቃይ ውስጥ ተውጦ።
መሞቱ በተሻለው ነበር።
③, ግፈኛ መሆን ያለውን መዘዝ።
ግፈኛ ሰው የቱንም ያክል ተመቸኝና አቅም አለኝ ብሎ ሌሎችን ቢበድል፤
በዚህች አለም ራሱ ቅጣቱን ይቀምሳል። በዚያኛው አለም ያለውንማ አላህ ይዞታል።
④, የሐጃጅ አሟሟት ትልቅ ውርደት ነው።
ተኝቶ እንኳ እንቅልፍ የለውም ነበር።
ሰውነቱ ሁሉ ተበክሎ ፓራላይዝድ ሁኖ ነበር የሞተው።
||
👉 ጽሑፌን እዚህ ላይ ልቋጨው።
እኛንም የቀደምት አበው ትውልዶችን ፈለግ ቀጥ አድርገን የምንከተል ሰዎች ያድርገን።
መቼም እናንተ እንኳ የረጅም ጽሑፍ ጥላቻ (Phobia) አለባችሁ፤ እኔ ስጽፍ የማይደክመኝን እናንተ ለማንበብ ይደክማችኋል።
የአላህ ፈቃዱ ከሆነ እንዲህ አይነት የቀደምት ደጋግ ሰለፎችን ታሪክ በማውሳት በቀጣይ ክፍሎች አስተያየታችሁንና የማንበብ ሁኔታችሁን አይቼ እመለሳለሁ።
እንዲህ አይነት እውነተኛ ታሪኮች ምናልባትም ዛሬ ላይ ከተቅዋ ተራቁታ የደረቀችውን ልባችንን፣ የማታነባውን አይናችንን፣ የተኛውን ህሊናችንን ለማርጠብና ለማንቃት ይረዱናል።
ሰለፎች ህይወታቸውን እንደት አሳለፏት ብለን እንመርምር።
ለማንኛውም እንደ ሁኔታችሁ አይቼ በቀጣይ ክፍል እስከምንገናኝ ሰላም ሰንብቱ።
ወስ-ሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱልሏሂ ወበረካቱህ።
ጽሑፉን ለሌሎችም ብታስተላልፉትና ሌሎችም አንብበው ቢጠቀሙ፤
ወደ ኸይር በማመላከታችሁ ምንዳን ትሸምታላችሁ።
||
ጽሁፉን ከሚከተሉት ድርሳናት ላይ ከከፊሎቹ ላይ ከፊል ታሪኩን፣ ከከፊሎቹ ላይ ደግሞ በብዛት ታገኙታላችሁ።
ሙሉ በሙሉ ግን አንዱ ላይ ብቻ አታገኙትም።
ሆኖም ግን እንዳይረዝም ብዬ (ረዝሞ የለም ወይ ባትሉኝ) የቀነስኳቸው ብዙ ሃሳቦች አሉ።
👉 ዋቢዎች፦
===========
✔️ ሒልየቱ-ል-አውሊያእ፡ 4/290-295
✔️ አል-ቢዳያህ ወን-ኒሃያህ፡ 9/107-108
✔️ ሲፈቱ-ስ-ሶፍዋህ፡ 2/51-54, 44
✔️ ሲየር አዕላም አን-ኑበላእ፡4/321
✔️ ታሪኹ-ጥ-ጦበሪይ፡ 4/23
✔️ ወፊያቱ-ል-አዕያን፡ 2/371
✔️ አን-ኑጁሙ-ዝ-ዛሂራህ፡ 1/228
✔️ አል-ሙንተዞም፡ 6/318
✔️ ሸዘራቱ-ዝ-ዝሃብ፡ 1/108
✔️ ታሪኹ ኸሊፋህ፡1/307
✔️ ጦበቃቱ ኸሊፋህ፡1/280
✔️ ጦበቃቱ ኢብኑ ሰዒድ፡ 6/256
✔️ ተራጂዑ አዕላሙ-ስ-ሰለፍ፡ ገጽ 47
♠
↑↓
ወንድማችሁ፦ ሙራድ ታደሰ
==========
ሙሐረም 27, 1441 ዓ.ሂ
መስከረም 15, 2012 E.C
September 26, 2019 G.C
||
የቴሌግራም ቻናሌን በመቀላቀል የምለቃቸውን መከታተል ትችላላችሁ።
Join: t.me/MuradTadesse