Translation is not possible.

በጨለማ ተጓዦችን… አበስራቸው‼

========================

✍ ምናልባትም ቀን ላይ ላብ ጠብ በሚያደርግ የጉልበት ሥራ ላይ አሳልፈህ ይሆናል፣ ናላን በሚያዞር የጭንቅላት ሥራ ተወጥረህ ይሆናል፣ በጠዋት የወጣህ ወደ ቤትህ የምትገባው አምሽተህ ይሆናል፣ ርቦህ ደክሞህ መጥተህ ትንሽ አረፍ እንዳልክ የፈጅር ሶላት ይደርስና በዙሪያህ ባሉ መስጂዶች «ሶላት ከእንቅልፍ በላጭ ነው፣ ኑ ወደ ሶላት፣ ኑ ፈላሕ ወደምትወጡበት መንገድ…» የሚል የጌታህን ጥሪ በአላህ ባሮች አንደበት ትሰማለህ።

ያኔ ነፍስህ በእንቅልፍ ሰመመን ውስጥ ሆና ከላይህ ላይ ያለውን ብርድልብስ አሽቀንጥረህ፣ ያንን ጣፋጭ እንቅልፍ ትተህ ለጌታህ ትዕዛዝ ምላሽ ለመስጠት ትነሳለህ ወይንስ «ቆይ ትንሽ እንቅልፌ ይውጣልኝና እነሳለሁ!» በሚል ሽንገላ ባልሰማ ጸጥ ብለህ ጸሐይ ሲወጣ መስገድ?  መቼም ከናካቴው አለመስገድ ይኖራል ብዬ አላስብም። አላህ ይጠብቀንና!

ፈጅር ላይ ከዚያ ደክሞህ ካገኘኸው ጣፋጭ እንቅልፍ ለመነሳት እነዚህ 3 ሐዲሦች በቂ ናቸውና ላስታውስህ ወደድኩ።

①ኛ) ለአንተ ገና ሳያዩህ በትካዜ የናፈቁህና  ሁሌም የሚቆረቆሩልህ አዛኙ ነቢይ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

(بشرِّ المشائينَ في الظلمِ إلى المساجدِ، بالنورِ التامِّ يومَ القيامةِ)

«በጨለማ ወደ መስጂድ ተጓዦችን የውመ-ል-ቂያማህ በሙሉ ኑር (ብርሃን) አበስራቸው።»

[ጃሚዑ-ስ'ሶጚር: 2129፣ ሶሒሕ አቡ ዳውድ: 561]

√ ያኔ የውመል ቂያማህ ሁሉም ሰው በጭንቅ ውስጥ ሆኖ፣ ታላላቅ ነቢያትና የአላህ መልዕክተኞች ﷺ ሳይቀሩ «ነፍሴ ነፍሴ» በሚሉበት ቀን፣ ከፊሉ ሰው በጸሐይዋ ንዳድ ላቡ እስከ አፍንጫው ድረስ ሲያሰምጠው፣ ወደየት ልሽሽ፥ ወደየት ልግባ በሚልበት የጭንቅ ቀን… «ሙሉ በሆነ ኑር» ከመበሰር የበለጠ ምን መታደል አለና ነው ፈጅር ሶላት ላይ የምትዘናጋው?

ይሄን ብስራት የነገረህ እኮ ተራ ሰው ሳይሆን የሁሉም ፈጣሪና ባለቤት የሆነው አላህ የላካቸው ውድ ነቢይ ﷺ ናቸው። በል ተነስ!

*

②) ነቢይህ ﷺ እንዲህም ብለዋል፦

(مَن صَلَّى الصُّبحَ فَهُوَ فِي ذِمَّةِ اللَّهِ…)

«ሱብሒን (የፈጅር ሶላትን) የሰገደ ሰው በአላህ ጥበቃ ስር ነው።»

[ሙስሊም: 657]

√ እና እንደ ሙስሊም በአላህ ጥበቃ ስር ከመዋል የበለጠ ምን መታደል አለና ነው የምንዘናጋው? አላህ በጥላው ስር ካዋለህ አንተን የሚዳፈር ሁሉ ጥላውን እንደተዳፈረ ነውና የሚከላከልልህ አላህ ነው። ምክንያቱም ራስህን ለርሱ ሰጥተሃልና! ያ ሊጎዳህ ያለ ሁሉ ከአላህ በታች የሆነ አንድ ተራ ፍጡር ነውና በጥበቡ አደብ ያሲዘዋል።

√ አዕመሽ እንዳስተላለፈው በአንድ ወቅት ሳሊም (የዐብደ-ል'ሏህ ኢብኑ ዑመር ልጅ) ከሐጃጅ አጠገብ ቆሞ ነበርና (ያው ሐጃጅ ኢብኑ ዩሱፍ እንደምታውቁት…) አንዱ በአጠገቡ ሲያልፍ አየና ሐጃጅ ለሳሊም "የዚህን ሰው አንገት በሰይፍ ቅላው!" ብሎ አዘዘው። ሳሊምም የታዘዘውን ለመፈጸም ሰይፉን እንዳነሳ… ለሰውየው «ፈጅርን ሰግደሃል?» አለው። አንገቱ ሊቀ'ላ የነበረው ሰውየም «አዎ» ሲል መለሰ። ሳሊምም «በል! እንዳሻህ ጉዞህን ቀጥል!» አለውና ወደ ሐጃጅ ተመልሶ ይዞት የነበረውን ሰይፍ ጣለው። ሐጃጅም ለሳሊም «አንገቱን ቀላኸው?» ብሎ ጠየቀው። ሳሊምም «በጭራሽ» አለው። ሐጃጅም «ለምን?» አለው። ሳሊምም «እኔ አባቴ (ዐብደ-ል'ሏህን ማለቱ ነው) ነቢዩ ﷺ "የጠዋትን (የፈጅርን ሶላት) የሰገደ ሰው እስከ ምሽት ድረስ በአላህ ጥበቃ ስር ነው!" ብለዋል ሲል ሰምቸዋለሁ።» ብሎ መለሰለት። «በአላህ ጥበቃ ስር ያለን ሰው አልዳፈርም!» ማለቱ ነው።

√ ታላቁ የዘመናችን ዐሊም ኢብኑ ዑሠይሚንም ይሄን ሐዲሥ አስመልክተው በሪያዽ ሸርሓቸው ላይ ትንታኔያቸውን ሲያሰፍሩ እንዲህ ብለዋል፦

" في هذا دليل على أنه يجب احترام المسلمين الذي صدَّقوا إسلامهم بصلاة الفجر ؛ لأن صلاة الفجر لا يصليها إلا مؤمن ، وأنه لا يجوز لأحد أن يعتدي عليهم)

«ይህ እነዚያን በፈጅር ሶላት እስልምናቸውን ያረጋገጡ ሙስሊሞችን ማክበር እንደሚገባ ማሳያ ነው። ምክንያቱም የፈጅር ሶላትን ሙእሚን እንጂ አይሰግዳትም። ስለሆነም ማንኛውም ሰው ድንበር ሊያልፍባቸው አይገባም።»

[ሸርሕ ሪያዹ-ስ'ሷሊሒን: 1/591]

ምንም እንኳ እስልምናችን በማንም ንጹሐን ላይ ድንበር ማለፍን ቢከለክልም፤ ጭራሽ በእንዲህ አይነት ባሮቹ ላይ ድንበር ማለፍን ደግሞ የክልከላ ጥግን ከልክሏል።

*

③ኛ) ሐቢቢ! የፈጅርን ሶላት ፈርዱን መስጂድ ሂዶ መስገድ፤ አይደለም ፈርዱን መስገድ ሱን'ናውን መስገድ ብቻውን ያለውን ደረጃ አልሰማህም? ወይንስ ሰምተህ መተግበር ተሳነህ?

ውዱ ነቢያችን ﷺ ምን እንዳሉ ልንገርህ፦

ሐዲሡን ያስተላለፈችው ራሷ ባለቤታቸው እናታችን ዓኢሻህ (እውተኛዋ የእውነተኛ ልጅ) ናት - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና። ውዱ ነቢይ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

(ركعتَا الفجرِ خيرٌ من الدُّنيا وما فيها))،

«የፈጅር 2 ረከዓዎች (ሱንናዎቹ)፤ ከዱንያና በውስጧ ካለው ይበልጣሉ።»

[ሙስሊም: 725]

وقال أيضًا እንዲህም ብለዋል ﷺ፦

 ((لهُما أحبُّ إليَّ من الدُّنيا جميعًا)

«እነርሱ ለኔ ከዱንያ ሁሉ የተወደዱ ናቸው።»

አስበው! ዱንያ ላይ ስንት ገንዘብና ስንት ስልጣን አለ?

በየሃገራቱ ያሉ ውብና ሃብታም መንደሮችን፣ ዘመናዊ መኪኖችንና መኖሪያ ቤቶችን፣ የቅንጦት መዝናኛዎችን… ስንቱን ልዘርዝርልህ። ስታየው የሚያስቀና ስንትና ስንት ነገር አለ። «እኛም ከነዚህ ጋር እኩል እዚህች ዓለም ላይ እየኖርን ነው?» የሚያስብሉ ስንትና ስንት ቅንጡ ኑሮዎች አሉ?

ግን ምን ዋጋ አለው? የፈጅርን እንኳን ፈርዱን ሱ-ን'ናውን መስገድህ ብቻ ከዚህ ሁሉ ይበልጣል። የሱን'ናው ትሩፋት እንዲህ ከሆነ ፈርዱ ምን ቢሆን ነው በአላህ!

ኧረ! ያ አኺ! ተነስ እንነሳና ፈጅርን እንስገድ! ደግሞ ለዚህች ለማትሞላና ብትሞላ እንኳ ነገ ጥለናት ለምንሄዳት ዱንያ ብለን ይሄን ሁሉ ትሩፋት እናስመልጥ እንደ?  ትንሽ ደቂቃ እኮ ናት ሐቢቢ! 24 ደቂቃ እንኳ ላትሞላ ትችላለች! ታዲያ እንደት ከ24 ሰዓቱ ውስጥ 24 ደቂቃ ለጌታህ ትዕዛዝ ምላሽ ለመስጠት አጣህ? የተፈጠርከው እርሱን ለመገዛት ሆኖ ሳለ ሙሉ ጊዜህን መስጠት ባትችል እንኳ 24 ደቂቃ መስጠት ተሳነህ? አስበው!

24 ደቂቃ በስንት እንደምታልፍ! ከጓደኛህ ጋ ሻይ ቡና እንበል ብለህ ስንት ሰዓታት ነው የምታሳልፈው? ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስንት ሰዓት ነው የምታሳልፈው? ኳስ… ገለመሌ እያልክ ምን ያክል ሰዓት ነው የምታሳልፈው? ታዲያ የባለዚሁ ሰው እንደት ይህቺን ታክል ደቂቃ ለሶላት መስጠት ከበደህ? ኧረ! ተው ሐቢቢ ተው! ብልጥ ሁን!

የላ! ፈጅር አዛን ሲል ወደ መስጂድ! የምን እየሰሙ መሟዘዝ! የምን አላርም አለመቅጠር ወይም የቀጠሩትን ማጥፋት!

አላህ ያግራልን! ውዶች አንዘናጋ! የፈጅርና የዒሻእ ሶላት ለሙናፊቆች ለማስመሰል እንኳ የማይመቹ የአማኝነት ማረጋገጫ ናቸውና እንበርታ። 

*

ለሌሎችም የፈጅር መስገድ መነሳሳት ሰበብ ከሆንን (ለአንድም ሰው ቢሆን) መልዕክቱን እናድርሳቸው።

||

ወንድማችሁ፦ ሙራድ ታደሰ

=========

Send as a message
Share on my page
Share in the group