1 year Translate
Translation is not possible.

ውበትን መጠበቅ በትዳር ውስጥ

           አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከትዳር በኋላ  ራሳቸውን ይጥላሉ። አንዳንድ ሴቶች ራሳቸውን በመጠበቅ ረገድ ከኒካህ በፊት የነበራቸው እና ከኒካህ በኋላ የሚኖራቸው ሁኔታ የሠማይና የመሬት ያህል ይለያያል። ይህ ከባድ ስህተት ብዙ ትዳሮችን የጦርነት ቀጠና አድርጓቸዋል። ወጣት ሴቶች ከትዳር በኋላ ከትዳር በፊት ከነበራቸው ልምድ በተሻለ ውበታቸውን ለመጠበቅ እና ለባሎቻቸው ዕይታ በመጉላት ላይ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ትዳር ውበታቸውን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ጋር የሚለያዩበት የመሰነባበቻ ድንበር አለመሆኑን መረዳት አለባቸው። እንድያውም ትዳር ከመቼውም ግዜ በበለጠ ውበት የሚጠበቅበት፣ ለትዳር አጋር ራስን ውብ አድርጎ ለማሳየት ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጥበት የአዲስ ህይወት መክፈቻ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በዚህ ጉዳይ ላይ አላህን መፍራትና የባሎቻቸውን ሀቅ መጠበቅ አለባቸው። 

መልካም ሚስት ባልዋ አላህን በማይፈቅደው ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ዐቅሟ የቻለውን ሁሉ ታደርጋለች። ዘወትር ራሷን ውብ በማድረግ ዓለሙን ሁሉ ረስቶ ዐይኖቹ በርሷ ላይ ብቻ ያጠሩ እንዲሆኑ ትተጋለች። በባልዋ ዐይን አስቃሚና ራሷን ያልጠበቀች ሆና ከመታየት የበለጠ የሚያስጠላትና የሚያስፈራት ነገር አይኖርም።

ትክክል ነው ባለቤትሽ ውብ ሁነሽ አጠገቡ ስትቀርቢ እርካታን ያገኛል። ደስታ ይሠማዋል። አላህ አንቺን ስለሠጠው አመስጋኝ ይሆናል። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን ውበትሽን በመጠበቅሽ የመጀመሪያው ተጠቃሚ አንቺው ራስሽ ነሽ። ውበትሽን ስትጠብቂ ስለራስሽ ያለሽ ግምት ከፍ ያለ ይሆናል። ጥሩ ይሠማሻል። ዘወትር ውብ ለመሆን መሞከር ውብ ነገር ነው።

ብዙ ሚስቶች ከትዳር ጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ ክብደታቸው ይጨምራል። ባል የሠውነት መገጣጠሚያቸው ለመለየት እስኪቸገር ድረስ ያለመጠን ይወፍራሉ። ራሳቸውን ለመጠበቅ የአመጋገብ ስርዓታቸውን ለማስተካከልም ሆነ በኢስላማዊ አዳብ በቤት ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ አይፈቅዱም። በአጭር ግዜ ውስጥ ባል ፍፁም ማየት የማይፈልገውን ገጽታ ይላበሳሉ። ውፍረት ውበትን ከመዋጡም በተጨማሪ ለጤና ችግር ያጋልጣል። ይህን ማወቅና መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

ፀጉር የሴት ልጅ ውበት ዋነኛ  መገለጫ ነው። ከትዳር በኋላ ፀጉርሽን ብዙ ግዜ የምትታጠቢበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። ይህም ስለሆነ ለፀጉርሽ የምትሰጪው አንክብካቤ ከትዳር በፊት ከነበረው ሁኔታ በብዙ መጠን መጨመር አለበት። ውሃ የሚነካው ፀጉር ብዙ እንክብካቤ ያስፈልገዋል።

አለባበስ ውበትን ያጎላል። ከባልሽ ጋር በሚኖርሽ ቆይታዎች ሁሉ አቅም በፈቀደ አለባበስሽ ዘናጭና ዓይኖቹን ከአንቺ ላይ የማያስነቅል መሆን አለበት። በቤት ውስጥ ከእርሱ ጋር ካለሽ በፍፁም ያረጁና ቆሻሻ ልብሶችን ከመልበስ ተጠንቀቂ። አዲስና ንፁህ  ልብሶች በባልሽ ፊት ካልለበስሻቸው ትርጉም የላቸውም። በቻልሽው መጠን በየግዜው አለባበስ ስልትሽን ቀያይሪ። አለባበስሽ ዘወትር አዲስ ሠው የሚመለከት ያህል እንዲሠማው የማድረግ ዐቅም ይኑረው።

ጠረን ነፍስን ያናግራል። ትዝታዎችን ይሸከማል። በባልሽ ፊት የሚኖርሽ ጠረን ልብን የሚሠረስር ጣዕም እንዲኖረው ጥረት አድርጊ። ሁልግዜ በጥሩ ሽታ ባልሽን ልትቀርቢው ይገባል። ይህን ለማሳካት በየዕለቱ መታጠብና ሽቶ መታጠን የሚያስፈልግ ከሆነ ከማድረግ ወደ ኋላ አትበይ። ሽቶሽ ግን በፍፁም ተከትሎሽ ከቤት እንዳይወጣ ጥንቃቄ አድርጊ። ውብ ጠረንሽ ማሽተት የሚፈቀድለት በአላህ ቃል የህይወት አጋርሽ የሆነው የባልሽ አፍንጫ ብቻ ነው።

በቤት ውስጥ የሚኖርሽን ጠረን ሁልግዜ ብዙም ሳትቸገሪ ጣፍጭ ሆኖ እንዲቀጥል ወጥ ቤት ስትገቢ የምትለብሺው ተለዋጭ ልብስ ማዘጋጀት ጠቃሚ ይሆናል።

ለህይወት አጋርሽ ውብና ንጹህ ለመሆን የምታደርጊውን ጥረት ሁሉ የአላህን ትዕዛዝ ለመፈጸም እንደምታደርጊው መልካም ስራ አስቢው። በእርግጥም የአላህን ውዴታ የሚያስገኝልሽ መልካም ስራ ነው። በአላህ ፈቃድ ይህ መልካም ስራሽ ጀነትን የሚያወርስሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የአላህ ቸርነት ሠፊ ነው።

Send as a message
Share on my page
Share in the group