Translation is not possible.

ሰለዋት እንድናበዛበት የታዘዝነው ነብይ ጀግንነቱ ሲወሳ

❀በአንድ ለሊት ላይ መዲና በጩኸት ተናወጠች። ሰሓባው ሁሉ ወደዚያ ድምፅ እየተንጋጋ አመራ። መጀመሪያ በቦታው ላይ ደርሶ አረጋግቶ እየተመለሰ ያገኙት ረሱልን ﷺነበር። አነስ (ረዐ) ይህን ሲተርክ እንዲህ ይላል፦

«የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከሰዎች ሁሉ መልካሙና ጀግናው ነበር ።የመዲና ነዋሪዎች የሆነች ለሊት ላይ ደነገጡ። ወደ (ረብሻው) ድምፅም ወጡ።የአላህ መልእክተኛም ዜናውን አረጋግጠው (አብርደው) አገኟቸው። በአቡ ጠልሓ ፈረስ ላይ ነበሩ።እርሱም ኮርቻ ያልተገጠመለት ነበር። ሰይፋቸውን ከፍ አድርገው «አትፍሩ ፤አትደንግጡ!» አሉ»

(ቡኻሪይ 3040)

ሰሃቦች ወደ ድምፁ እየሄዱ ነው። ረሱልﷺ ግን ከድምፁ ቦታ እየተመለሱ!የህዝብ መሪ እንዲህ ነዋ!

አነስ (ረዐ) ኮርቻ ያልተገጠመለት ሲል ማለት የፈለገው በአደጋ ጊዜ ፕሮቶኮል ሳያበዛ ራስን ለመፍትሄ አቻኩሎ መብረርን ለመግለፅ ነው። ልክ በአስቸኳይ ችግር ጊዜ ሄልሜት ምናምን ሳትፈልግ ሞተር አስነስቶ እንደ መክነፍ።

❀በታላላቅ ፍልሚያዎች ላይ ረሱል ﷺ የጠላት ታርጌት ቢሆኑም እርሳቸው ግን ማንነታቸውን ሳይደብቁ ስማቸውን ሁሉ በግልፅ እየተናገሩ ወደፊት ይገሰግሱ ነበር።ከነዚህ ማሳያዎች አንዱ የሑነይን ዘመቻ ነው።

በዚህ ዘመቻ የሀዋዚን ጎሳ ቀስቶች ከባድ ስለነበሩ ሰሃባዎች ሸሽተዋል።

«ለበራእ ኢብኑ ዓዚብ (ረዐ) «የሑነይን እለት ሸሽታችኋል?» ተብሎ ተጠየቀ።እርሱም «የአላህ መልእክተኛﷺ በጭራሽ አልሸሹም ነበር። አቡሱፍያን ኢብኑል ሓሪስ የበቅሏቸውን ልጓም ይዞላቸው ነበር። ሙሽሪኮች ሲከቧቸው ወረዱና «እኔ ነብዩ ነኝ ውሸት አይደለም! እኔ የዐብደል ሙጠሊብ ነኝ!» አሏቸው። የዚያን ቀን  ከርሳቸው የበለጠ ብርቱ (ጀግና) ሰው አልታየም»

(ቡኻሪይ 3042)

❀100% ሞት በሚጠረጠርበት ቦታ ላይ ጀግንነትን እና በአላህ ላይ እርግጠኝነትን አረጋግጠዋል!

ጃቢር (ረዐ) ይተርካል ፦

« ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ጋር የነጅድን ዘመቻ ተካፈልን። የቀትር እንቅልፍ ሰአት ላይ ሲደርሱ ዛፋማ በሆነ ደን ውስጥ ሳሉ ከአንዲት ዛፍ ጥላ ስር አረፉ።

ሰይፋቸውንም አንጠለጠሉና በጥላዋ ተጠለሉ። ሰዎችም በየዛፉ ስር ተለያይተው ተጠለሉ። በዚህ ሁኔታ ሳለን ድንገት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ጠሩንና ሄድን።አንድ ገጠሬ ከፊት ለፊታቸው ተቀምጧል። እንዲህ አሉን፦

«ይህ ሰው ተኝቼ ሳለሁ መጥቶ ሰይፌን መዘዘ። ስነቃም በስለቱ በኩል ይዞት ጭንቅላቴ ላይ ቆሟል። «ከኔ ማን ያድንሃል?» አለኝ። እኔም «አላህ!» አልኩት ።ሰይፉን ወደሰገባው አስገባውና ተቀመጠ ፤ እርሱም ይሄ ነው» አሉ። »   (ቡኻሪይ 4139)

ሰይፉን በስለቱ (በፍላፃው) በኩል መያዙን የገለፁት ሰውዬው ከምላሻቸው በኋላ መግደል የሚችልበት አቋም ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው። የተቀባበለ ሽጉጥ ላይ ጣቱን ምላጩ  ላይ ያደረገ ሽፍታ ፊት በየመን ደን ውስጥ ሆነህ ምን ልትመልስ እንደምትችል መሳል ነው።

ይህ የጀግንነትና የየቂን ጥግ ካልሆነ እዚህ ምድር ላይ ጀግንነት የለም!

❀በጦርነት መሃል የመሳሪያ ነውጥ ድብልቅልቅ ሲል ሰዎች ካጠገቡ የሚሸሸጉበት ነብይ፦

ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ (ረዐ) እንዲህ ይላል፦

«ጦርነት ሲጋጋምና ሰው ለሰው ሲተላለቅ በአላህ መልእክተኛ ﷺ እንሸሸግ ነበር።ከኛ አንድም ሰው ወደ ጠላት ቅርብ የሚሆን የለም እርሳቸው ቢሆኑ እንጂ።»

(ሙስነዱ አሕመድ 1347)

ሰሃባዎች ከጀርባው የሚከለሉ ከሆነ አስከላዩ  ከጠላት ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ነው ማለት ነው። እርሱ የዐብደላህ ልጅ ሙሐመድ ነው!  ሰለዋቱ ረቢ ወሰላሙሁ ዐለይሂ! 

❀በመካው ዘመን ቢሆንም አዛዎችን ሁሉ ታግሰው ያሳለፉት እንዲታገሱ ስለታዘዙ እንጅ የፍርሃት አልነበረም ።የዚህም ማረጋገጫው ፦

«የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከመስጅድ (ሐረም) እየወጡ ሳለ አቡ ጀህል ከፊት ለፊታቸው መጣ ። መልእክተኛውﷺ እጁን ያዙትና አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ወዘወዙት፤  ወየውልህ ከዚያም ወየውልህ! አሉት። እርሱም «ታስፈራራኛለህ? እኔኮ የዚህ(የመካ) ሸለቆ ሊቅና የተከበርኩ ሰው ነኝ»  አላቸው ።

(ተፍሲሩል ቁርጡቢይ) 

የቱ ጀግና ነው? አንድም የሚጠጋበት ሃይል ሳይኖረው የሀገር አስተዳዳሪን ወዝውዞ የሚዝትበት? !

❀ጠላት ህዝብን ብቻውን የተጋፈጠ ነብይ ፦

ረሱልﷺ የመካን ህዝብ በብቸኛነት የዳዕዋ ስራ ተጋፍጠዋል።ጥሪያቸውን የሚጠሉ መሪዎች ፊት ለአላህ ሱጁድ ያደርጉና ይሰግዱ ነበር።ይህ የድፍረትና የጀግንነት ጥግ እንጂ ሌላ አይደለም።

አነስ (ረዐ) ይተርካል ፦

«የአላህ መልእክተኛን ﷺአንድ ቀን (ሙሽሪኮች) ደበደቧቸው ራሳቸውን እስኪስቱ ድረስ።አቡበክርም ቆመና እየተጣራ መጣ፤ ወየውላችሁ አንድን ሰው ጌታዬ አላህ ነው ስላለ ትገድሉታላችሁ??!» አላቸው።ማነው ይሄ ደግሞ ? በማለት ተጠያየቁ። እብዱ አቡበክር ነው ተባባሉ»

(ዘዋኢዱ ፈዳኢሉ ሰሃባህ 218)

የረሱል ﷺጀግንነት ብቻቸውን ሆነው የከተማን ህዝብ ነው የተጋፈጡት! ይህ የድፍረት ውሃ ልክ እንጅ ሌላ አይደለም።አቡበክርን ተማምነው ነው እንዳይባል አቡበክር ራሱ የደረሰላቸው ራሳቸውን ስተው ነው።

ይህ ማለት ረሱል ﷺ የተጋፈጡት ብቻቸውን ነው! በመካው ህይወታቸው ትእግስት ያየለው በአላህ ትእዛዝ መሰረት እንጅ ከፍርሃት አለመሆኑን ማረጋገጫም ነው።

በዚህ ክስተት አቡበክር ለረሱል ﷺአግዞ  እስከመጨረሻው ከህዝብ ጋር ተፋልሟል።አቡከክር ሙሽሪኮች ፀጉሩን እስኪነጫጩት ድረስ ታግሉ ራሱን ስቷል።

ከነዚህ ውጭ የረሱል ጀግንነት የተገለጡባቸው ክስተቶችም አሉ። አላህ በጀነት የርሳቸው ጎረቤት ያድርገን!

❀በእናታችን ዓኢሻህ ንግግር እንጨርስ። እናታችን (ረዐ) እንዲህ ትላለች፦

«የአላህ መልእክተኛ ﷺ አገልጋያቸውን ወይም ሴትን ወይም ሌላን ነገር በጭራሽ መትተው አያውቁም።በአላህ መንገድ ትግል ላይ ካልሆነ በቀር።ከርሳቸውም በክብራቸው ተመጥቶባቸው ተበቅለው አያውቁም።የአላህ ድንበር ከተጣሰ ሲቀር (ያኔ) ለአላህ ዐዝዘ ወጀል ይበቀላሉ»

(ሙስሊም 2328)

የረሱልን ባህሪ በከፊሉ አምነህ በከፊሉ አትካድ! ረሱል ለሚታዘንለት አዛኝ ለሚቀላው ደግሞ ሰያፍ ነበሩ!

Send as a message
Share on my page
Share in the group