ከአላህ ጋር ነግዶ ማን ከሰረ?!
(እውነተኛ ድንቅ ታሪክ)
💎💎💎💎💎💎💎💎💎
Mahi Mahisho
🔹🔹🔹🔹🔹
በሰባዎቹ መጀመሪያ በሀገረ ግብፅ ግዛት ተፈህና አል-አሽረፍ በምትሰኝ ትንሽዬ መንደር ውስጥ ምንም የሌለው ደሀ የግብርና መሃንዲስ ጣራዋ በተቀደደ፣ ግርግዳዋ በተፈረፈረ ደሳሳ የጭቃ ቤት ውስጥ ከወላጆቹ ጋር ጎጆውን ቀልሶ ይኖር ይዟል። ግርግዳው በጋዜጣ የተሸፈነ ቤት!! በወላጆቹ ልፋት ተምሮ ለወግ ማዕረግ በቅቶ ቢመረቅም ስራ ማግኘት ግን አልተቻለውም። ሰላህ አጢያ ይሰኛል። ያረጀ እንጂ አዲስ ልብስ ለብሶ አያውቅም። ትክክለኛው የጫማ ቁጥር 42 ቢሆንም ከቆሻሻ ገንዳ ያገኛትን 44 ቁጥር ጫማ እንዳታልቅበት በቀስታ እየረገጠ ይጓዝባታል።
በግብርና ፋኩሊቲ ተመርቀው በከፋ ድህነት የሚሰቃዩ፣ ስራ ለመጀመር የሚፈልጉ ዘጠኝ የመንደራቸውን ሰዎች ሰብስቦ አነስተኛ ፕሮጀክት ለመጀመር ወሰነ። አማከራቸው ተስማሙ። አስረኛ አጋር እየፈለጉ እያንዳንዳቸው 200 የግብፅ ፓውንድ አዘጋጅተው ጠበቁ።
ተሰብስበው ሻይ እየጠጡ ወደነበሩት አጋሮቹ ዘንድ አቀናና "አስረኛውን አጋር አግኝቻለሁ" አላቸው።
"ማን እነደሆነ ንገረን" ሲሉ ጠየቁ
"አላህ ነው" በማለት መለሰላቸው። "ገንዘባችንን ከአደጋ ለመጠበቅ፣ ኃብታችንን ለማፋፋት እርሱ አንደኛው አጋራችን ይሆናል" በማለት ንግግሩን አከለ። ሁሉም ተስማሙ።
በጋራ የተቋቋመው የህብረት ኩባኒያ ውሉ ፀድቆ "አስረኛው ባለድርሻ አላህ የትርፉን አንድ አስረኛ ይወስዳል" የሚለው ቃል ከውሉ ወረቀት ላይ ሰፍሮ ሁላቸውም ፊርማቸውን አኖሩ። እውነተኛ የህብረት ስራ፣ ግልፅ ስምምነት ተደረገ።
የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ውጤት ጥሩ ትርፍና የተለየ ምርት ማስተናገዱን ሲመለከቱ ለተገኘው ትርፍ ለአላህ ምስጋና ይሆን ዘንድ የምርት ዑደት ውጤቱን "የታላቁ አጋር ድርሻ" በሚል መጠኑን ለመጨመር የአላህን ድርሻ ወደ 20% ለማሳደግ ወሰኑ። በየአመቱ ከፍ እያለ የአላህ ድርሻ 50% ደረሰ። አርሰው ቡቃያውን ወቅተው ምርቱን ይሸጣሉ። ነግደው ካተረፉት የአላህን ድርሻ ሳያጓድሉ ሀቁን ጠብቀው ትክክለኛ ቦታ ላይ ያውላሉ።
መስጂዶች፣ የሴቶች ሒፍዝ ማዕከል የአይታሞች ማደርያ የአቅመ ደካሞች መመገብያ ተቋማትን በአላህ ድርሻ ገነቡ። ትርፉ እያደገ ሲመጣ ለመሳኪኖች የዕርዳታ ድርጅትን አቋቋሙ..
በግብፅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ትንሽዬ መንደር ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ አራት ኮሌጆችን ገነቡ። እያንዳዳቸው ለ600 ተማሪዎች የሚሆን ማደርያ 1000 ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ኮሌጆች!
ማንኛውም የኮሌጁ ተማሪ ወደ ቀዬው ለመሄድ ሲፈልግ ነፃ ትኬት ማግኘት እንዲችል በይተል ማል የሚል ቢሮን አቋቋሙ።
በመንደሩ ደሃ እስኪጠፋ ተቋሙ ፋፋ። ኸይራቱ ወደ ጎረቤት መንደሮች ጭምር ዘለቀ። ስራ አጥ ወጣቶች ከድህነታቸው ተላቀው እንዲሰሩ ተመቻቸላቸው። ለጎረቤት ሀገራት አትክልቶችን ኤክስፖርት ማድረግ ጀመሩ። ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ለከተማዋ ነዋሪ ከትልቅ እስከ ትንሹ የአትክልት ከረጢት በስጦታ ይበረከትላቸው ገባ።
በረመዳን የመጀመሪያዎቹ ቀናት ኢፍጣር ተዘጋጅቶ ወንዶች በአደባባይ ሴቶች በየቤታቸው በፍቅር በአብሮነት ተሰብስበው ያፈጥራሉ። ወላጅ አልባ ሴቶች ለትዳር ሲደርሱ ወጪያቸው ተሸፍኖ ይዳራሉ።
ይህ ሁሉ በአላህ ድርሻ የሚሰራ መልካም ተግባር መሆኑ ያስገረማቸው መስራቾቹ የፕሮጀክቱ ባለቤትነት ወደ አላህ እንዲዞር ወሰኑ። እነርሱም የአላህ ሰራተኛ የረቢ አገልጋይ ሆኑ። ባለቤትነቱን ወደአላህ ሲያዞሩ "ትርፉ ሳይቋረጥ ድሆች ይጠቀሙ ዘንድ ጌታችን ሆይ አደራ!" የሚለውን ቃል ከውሉ ወረቀት ላይ አሰፈሩ።
አትራፊ ንግድ!!
መልካም ግብይይት!!
"አላህ ከምእምናን ነፍሶቻቸውንና ገንዘቦቻቸውን ጀነት ለእነሱ ብቻ ያላቸው በመኾን ገዛቸው" ይሉሀል ይህ ነው።
ኢንጂነር ሰላህ አጢያ በ70 አመታቸው በጉበት በሽታ ሲሰቃዩ ቆይተው እንደ አውሮጳውያን የዘመን ቀመር ጥር 11 ቀን 2016 ሩሐቸው ከጀሰዳቸው ተላቀቀች። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ጀናዛቸውን ሸኘ። እየተላቀሱ ጀሰዳቸውን ከለህዱ አሳረፉ። ልጅ አልነበራቸውም።
አላህ ከምህረቱ አጎናፅፎ ጀነተል ፊርደውሱን ይወፍቃቸው።
╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍╍
ምንጮቼ:-
- الشيخ خالد الجندي ينعي صلاح عطية نسخة محفوظة 25 فبراير 2020
- تفهنا الأشراف قرية بلا عاطل أو فقير نسخة محفوظة 17 مايو 2017
- صلاح عطية رجل أعمال تاجر مع الله نسخة محفوظة 12 مايو 2017 على موقع واي باك مشين