Translation is not possible.

በአጎራባች አካባቢዎች ይሰማ የነበረው የሰዎች እገታ ወደ መሀል ከተማ ገብቶ ሰላማዊ ሰዎች እየታገቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተጠየቁ ነው:: አጋቾቹ የጠየቁትን ገንዘብ ባሉት ወቅት ካልተሰጣቸው ያለምንም ርህራሄ እና ማቅማማት ያገቱትን ሰው በመግደል አስክሬኑን ጥለው ይሰወራሉ::

ከዚህ ቀደም ወንጀለኞች ሰዎችን የሚያግቱት የሚፈልጉትን ገንዘብ ለመቀበል ነበር:: የጠየቁት ገንዘብ እስኪሰጣቸውም በመዛት እና በማስፈራራት ቆይተው ገንዘቡን ሲያገኙ ያገቱትን ሰው ይለቁ ነበር:: አሁን ግን የእገታው አላማ ምን እንደሆነ ግራ አጋቢ ሆኗል:: በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይጠይቃሉ፣ ገንዘቡ ተፈልጎ እንኳን እስኪ ሰጣቸው አይጠብቁም:: ያገቱትን ሰው ገድለውት ይሄዳሉ::

ይህ እገታ ህዝቡን ለማሸበር ይሁን ለዝርፊያ ግልፅ አይደለም:: በሚሊዮን የሚቆጠር ገዘንብ ይጠይቁና በቀናት ውስጥ ያገቱን ሰው ይገድሉታል::

ወንጀል በስፋት ይሰራበታል በምትባለዋ በደቡብ አፍሪካ እንኳን አጋቾች የጠየቁትን ገንዘብ ተደራድረው ተቀብለው ያገቱትን ሰው ይለቃሉ:: የእኛ ሀገሮች ግን ዋና አላማው ግድያ በሚመስል መልኩ ነው ያለምንም ጊዜ ያገቱን ሰው ህይወቱን የሚያጠፉት::

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በመሀል የሀገሪቱ መዲና የዚህ መሰሉ ወንጀል በስፋት እየተፈፀመ ለምን ዝምታን እንደመረጡ ግራ አጋቢ ነው:: በየክፍለሀገሩ በየጫካው ሰላማዊ ዜጎች ሲታገቱ ሽፍቶች ናቸው ያገቷቸው እየተባለ ይሸፋፈን ነበር:: ዛሬ ግን ይህ እገታ መሀል አዲስ አበባ እየተፈፀመ ነው::

የመንግስት ትንሹ ኃላፊነቱ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው:: የፀጥታ ኃይሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እያበለፀግነው ነው ተብሎ እየተነገረን በመዲናዋ እንብርት ዜጎች እየታገቱ በሚሊዮን ገንዘብ ሲጠየቁ እና ሲገደሉ ማየት ያስገርማል::

የሚመለከተው የመንግስት አካል ይህ ወንጀል ተስፋፍቶ የስራ እድል መስሎ የሚታይበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ከራሱ ጉያ ያሉትን ወንጀለኞችንም ጭምር ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነቱን ሊያስከብር ይገባል::

Send as a message
Share on my page
Share in the group