Translation is not possible.

« ምን ያወጉ ነበር? »

ሌት ተቀን በሒክማ ወደ አላህ ሲጣሩ

ከእስትንፋሱ የወጣው ምን አለ « አየሩ »?

አንጀታቸው ታጥፎ ድካማቸው ሲያይ

ርቧቸው ያሰሩት ምን አለ ያ « ድንጋይ »?

መንገዱን ለመዝጋት ሰርክ የሚጣሉ

ሊጎዱት ሲታጩ « እሾኾች » ምን አሉ?

ወዳጃቸው አጥተው በሀዘን ሲዋጡ

« እንባዎች » ምን አሉ ’ካይናቸው ሲወጡ?

መዓዛው የለመደው የኹጥባው « ሚንበሩ »

ምን ተሰምቶት ይሆን ሲርቀው ኸበሩ?

ናፍቆት ፍቅሩን ይዛ ክብር የታደለች

ሽሽግ ያረገችው « መዲና » ምን አለች?

ለፍቅሩ ሊሰዋ ሸሂዱ ሲቀርባት

« መደቧ » ምን አለች አሊ ሲያርፍባት?

ጧኢፍ የነበረ « ድንጋይ ዱላ » ሁሉ

ምን ተሰምቶት ይሆን ሲያርፍ ከአካሉ?

በድር ላይ በዱዓ አላህ ሲማፀኑ

ምንድን ተባባሉ « ንፋስ እና ቀኑ »?

ከፍ ሊሉ

ዝቅ ሲሉ

በሩኩዕ ጎንብሰው ሱጁድ ላይ ሲደርሱ

ትንፋሹ የደረሰው

እንባው የዳበሰው

ገላው ለሸፈነው

ምን ብሎ አወጋው ያ « መሬት ለልብሱ »?

በገደል በሜዳው ከጋጣው የዋሉ

በእሱ የተጠበቁ « ፍየሎች » ምን አሉ?

ሲርበው ሲጠማው ሲታጠፍ አንጀቱ

ባዶ ሆዱን ሲያድር ምንድን አለ « ቤቱ »?

ገላው ሰንበር ስሎ ሲታይ ምልክቱ

ጎኑ ምቾት ሲያጣ ምን አለ « ውበቱ »?

ለፍቅር ናፍቆቱ ለሀዘን ብሶቱ

ቃል እየመረጠ ባለ አንደበቱ

በድርሳን አስፍሮ የውስጡን ሲያሰማ

ትዝታ ያለበት

ቃል የሌለው ግዑዝ አንዴም አልተሰማ።

ግና…

እንዴት ነበር ’ሚሆን ቃል ቢያውቁ ግዑዛን

ምን ያወጉ ነበር ስለዛ የሰው ሚዛን?

ብቻግን…

ውስጡን ላልገለጠ

ቃልም ላልመረጠ

ፍቅሩን ላሰፈረ

በመራቅ ላፈረ

ለሁሉም እንዲሆን ሁሌም ባ’ለም ደጃፍ

ሁሉም እንዲግባባ እንዲህ ተብሎ ይፃፍ!

«ሙሀመድ ትልቁ፣ የፍጥረታት እንቁ

ታውቀው አይሰለቹ፣ ተገልፀው አያልቁ።»

[አብዱልሀኪም ሰፋ ]

Send as a message
Share on my page
Share in the group