Translation is not possible.

እስራኤል የአል-ሺፋ ሆስፒታልን በዒላማ ውስጥ ያስገባችው ለምንድነው?

------

አፈንዲ ሙተቂ

------

በጋዛ ከተማ መሀል የሚገኘው "አል-ሺፋዕ" ሆስፒታል በዓለም ሚዲያ ስሙ በሰፊው እየተነሳ ነው። ይህም የሆነው እስራኤል "የሀማስ ኮማንድ ፖስት በሆስፒታሉ ውስጥ አለ" በሚል ማመካኛ የጦር ኃይሏን ወደ ሆስፒታሉ አስገብታና ታካሚዎችን፣ ሀኪሞችን፣ ሰራተኞችንና በሆስፒታሉ የተጠለሉ አንድ ሺህ ያህል ንጹሐን ሲቪሎችን እያንገላታች በመሆኑ ነው።

በእውነት ሆስፒታሉ የሃማስ ኮማንድ ፖስት ነውን?

-----

ስለሆስፒታሉ በጥልቀት የሚያውቁ የጋዛ ነዋሪዎችና በሆስፒታሉ ዙሪያ መረጃ ያሰባሰቡ ወገኖች የሀማስ ኮማንድ ፖስት በሆስፒታሉ ግቢ እንደሌለ መስክረዋል። እስራኤል ሆስፒታሉን የምትደበድበው እና ዓለም አቀፍ ህግን በተጻረረ ሁኔታ የጦር ኃይሏን ወደ ግቢው ያስገባችው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

=> አል-ሺፋ ሆስፒታል በጋዛ ካሉት ሆስፒታሎች ሁሉ ትልቁ ነው። በዕድሜውም ከአህሊ ዐረብ ሆስፒታል ቀጥሎ ሁለተኛው ነው። ሆስፒታሉ የተቋቋመው እስራኤል ከመመሥረቷ በፊት ነው። በመሆኑም በታሪካዊነቱ በፍልስጥኤም የአደራ አስተዳደር (Mandatory Palestine) ዘመን የነበረውን ሁኔታ ይመስክራል። እንግዲህ እስራኤል ታሪካዊነቱን ዋጋ ቢስ ለማድረግ ስትል ነው አል-ሺፋ ሆስፒታልን ድምጥማጡን ለማጥፋት የወሰነችው።

2. ሁለተኛው ምክንያት አሁን በጋዛ የቀረው መንግሥት እንደ ኮሚኒኬሽን ቢሮ የሚጠቀምባቸው ክፍሎች በሆስፒታሉ ህንጻ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ነው። ይህ ቢሮ የእስራኤልን ወንጀሎች እያጋለጠ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም እርሱን ጸጥ ለማድረግ ስትል ጦሯን ወደ ሆስፒታሉ አስገብታለች።

3. ከሁሉም በላይ ግን የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር የጋዛ ቅርንጫፍ በሆስፒታሉ ዋና ህንጻ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው ሆስፒታሉን የእስራኤል ዒላማ ያደረገው። እንደሚታወቀው የእስራኤል ጦር በየቀኑ በጋዛ የሚገድላቸውን ሲቪሎች (በተለይም ሕጻናት እና ሴቶች) መረጃ እያጠናቀረ በዓለም ዙሪያ የሚያሰራጨው ይህ የጤና ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ነው። እርሱ የሚያሰራጫቸው መረጃዎች አስተማማኝ መሆናቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተረጋግጧል። በዚህም የተነሳ የጋዛው የጤና መምሪያ የሚሰጣቸውን መረጃዎች የሚሰብስቡ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ሪፖርተሮች በሆስፒታሉ ግቢ መገኘታቸው የየዕለቱ ትእይንት ሆኗል።

እስራኤል በውጊያው መስክ የበላይነትን ብትይዝም በፕሮፓጋንዳው መስክ የትም መድረስ አልቻለችም። ከዓለም ሕዝብ አብዛኛው እጅ ጭካኔዋን በደንብ ተረድቷል። የእስራኤልን ጭካኔ እያጋለጡ ካሉት ትልቅ ተቋማት አንዱ በፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር የጋዛው ቅርንጫፍ ነው። በመሆኑም የዚህን መስሪያ ቤት ሰራተኞች አንደበት ለመዝጋት ስትል በታንክና በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ጭምር ወደ አል-ሺፋ ሆስፒታል ቅጽር-ግቢ ገብታለች።

-------

የጋዛው ጭፍጨፋና ጦርነት አርባኛ ቀኑን ይዟል። እስራኤልም በዘር ማጥፋት ዘመቻዋ ቀጥላለች። ሀማስም ሮኬቶቹን መተኮሱን ቀጥሏል። የእስራኤል እብሪት የት እንደሚያደርሳት አናውቅም። ፈጣሪ የፍልስጥኤምን ሕዝብ ከገጠመው ፈተና እንዲታደገው እንማጸናለን።

------

አፈንዲ ሙተቂ

ህዳር 5/2016

Send as a message
Share on my page
Share in the group