Follow & Share → Umma ሚዲያ
↓↓↓↓↓
ሒጅራ 15ኛው አመት ላይ ሰሓባዎች የዐረብያን ምድር በአንድ
ስረወ መንግስት የሚተደደር ግዛት አድርገውት በአቡ በክር
አማካይነት ተቆጣጥረውታል።
ሰሀባዎቹ በነቢ ሰዐወ መሞት ያነቡት እንባ ባይነጥፍም
ስሜታቸውን ዋጥ አድርገው ዘመቻዎችን እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በሳዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስ የሚመራው ክፍለ ጦር 30,000 የነቢ
ሙሪዶችን ይዞ ከዒራቅ መግብያ ከሚገኘው ሜዳ ላይ ተሰልፏል።
ያኔ ዒራቅ በፐርሺያን ስረወ መንግስት ውስጥ የምትገኝ ግዛት
ስትሆን የነቢ ሙሪዶችን ለመጋፈጥ 200,000 ሰራዊቶችን እና
33 የጦር ዝሆኖችን በጦር መሪያቸው ሩስቱም አማካይነት
አሰልፈዋል።
የምድራችን ሁለቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስረወ መንግስቶች
ሰራዊቶቻቸውን አሰልፈው ውግያ ሳይጀምሩ ለተወሰኑ ቀናት ማዶ
ለ ማዶ ሲፈጠጡ ከረሙ።
«መልዕክተኞቻችሁን ላኩልን'ና እንግባባ» የሚል መልዕክት
ከፐርሺያው ጦር አዛዥ ወደ ሰሀባው ሳዕድ ተላከለት።
ሳዕድ'ም ከጀግኖቹ መሀል ሪብዒይ የተሰኘውን ሙሒብ መርጦ
ወደ ፐርሺያውያኑ የጦር ካምፕ ላከው።
ሪብዒይ መልከ መልካም እና የወንድነት ወኔ ከፊቱ የሚነበብ
ብርቱ ሙጃሂድ ነው። ከፈረሱ ጀርባ እየከነፈ ከካምፑ ደረሰ።
ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰራዊቶች ተሰልፈዋል፣ በርካታ የጦር
መገልገያዎቻቸው ዝግጁ ሆነው በየቦታዎቻቸው ተቀምጠዋል።
ዐረቦቹ የማያውቋቸውን የጦር መገልገያዎች በየቦታው
ቢመለከተውም ግድ ያልሰጠው ሪብዒው የፈረሱን ልጓም
ወደተላከበት ለጎመው።
የጦር አዛዡ ከሚገኝበት ድንኳን ደረሰ። በአንፀባራቂ መጋረጃዎች
የተሽሞነሙነው ድንኳን በውስጡ ባለ ጌጥ ትራሶች እና
ምንጣፎች ተነጥፈውበት አይቶት የማያውቀውን የቤት ውስጥ
ጌጦችን ተመለከተ።
የነቢ ሙሪድ ዱንያ ምን ገዶት! ከአፈር ተቆፍረው ለሚወጡ
የማዕድናት ጌጥ መማረክን ነቢም አላስተማሯቸውማ!
ሪብዒይ ከፈረሱ ጀርባ ከነግርማ ሞገሱ ተሰይሞ የድንኳኑን
መግብያ ዘልቆ ገባ። የጦር አዛዡ የወርቅ ዘውዱን ከራሱ ላይ
ደፍቶ በዙፋኑ ላይ ሁኖ በአግራሞት ይመለከተዋል።
ሪብዒይ የተንኳሰሰች ልብሱን ለብሶ፣ ሰይፉን ከወገቡ ታጥቆ፣
ከድንኳኑ ስር በተነጠፈው ምንጣፍ የተወሰነ ርቀት በፈረሱ ከሄደ
በኋላ ፈረሱን ከወርቃማው ትራስ ላይ ሸብ አድርጎ ወደ ዙፋኑ ሄደ።
ከዙፋኑ ዙርያ ከተሰለፉት ጠባቂዎች አንዱ አስቆመው'ና፦
«ትጥቅህን እዚህ ጋር ፍታ» አለው።
ፍርሀትን መች ያውቅና! ፈሪ አላሰለጠነው'ማ!፦ «ስማ እኔ ትጥቄን
ስታዙኝ ልፈታ አይደለም እዚህ የመጣሁት። ጠርታችሁኝ
መጥቻለሁ ከነ ትጥቄ መግባት ከከለከላችሁኝ መመለስ
እችላለሁ» ብሎ መለሰለት።
«ተዉት ይምጣ ከነ ትጥቁ» አለ የጦር አዛዡ ሩስቱም ከዙፋኑ ላይ
ተደላድሎ ቁልቁል እየተመለለታቸው።
ሪብዒይ ከቆመበት ጀምሮ እስከ ዙፋኑ ድረስ የተደረደሩትን የጌጥ
ትራሶች እና የንጉሳን ምንጣፎችን በአሸዋማ ጫማው እየረገጠ
ከዙፈኑ ፊት ቆመ።
«ለምንድነው እዚህ ድረስ የመጣችሁት?» ብሎ ጠየቀው የጦር
አዛዡ። የዐረቢያ ነገዶች ለልመና እንጂ ለጦር የፐርሺያን ምድር
ሲረግጡ ተስተውለው ስለማያውቁ።
የቀድሞው ታሪኩ ምንም አላሸማቀቀውም። ገጠሬነቱ ባጎናፀፈው
የወኔ ገፅታ ቀና ብሎ፦ «አላህ ልኮን ነው። አላህ ፍጡራንን
ከፍጡራን አምልኮ ነፃ አውጥተን ወደ ፈጣሪ አምልኮ እንድናስገባ፣
ከዱንያ ጥበት ወደ ሰፊው ኢስላም፣ ከሀይማኖቶች አድሎ ወደ
ፍትሀዊው ኢስላም እንድናሸጋግር ልኮን ነው።
ይህን ይዘን መልዕክቱን ለሰው ልጅ በሙሉ እናስተጋባለን። ይህን
የተስማማ ተስማምተነው ትተን እንመለሳለን፤ አሻፈረኝ የሚል ካለ
ተጋድለነው ከጌታው ፊት ይዘነው ለፍርድ እንቆማለን።»
በመጨረሻም ቃል ከገቡ የማያፈገፍጉ የኑረል ካኢናቱ ሙሒቦች
በቃል ኪዳናቸው መሰረት ለክፍለ ዘመናት አለምን የገዛውን ስረወ
መንግስት በጣት በሚቆጠሩ ቀናት እንደ ወደመ አውድማ
አድርገው ፈጇቸው። ሀገራቸውንም ተቆጣጥረው ከግዛታቸው
አካለሉ።
"የደረሳውን ማንነት ልታውቅ ኡስታዙን ተመልከት" እንደሚሉት ሁላ
የሰሀባዎቹን ማንነት ለማወቅ ነቢን ሰዐወ መመልከት በቂ ነው።
_________
ምንጭ፦
ﺍﻟﺒﺪﺍﻳﺔ ﻭﺍﻟﻨﻬﺎﻳﺔ ﻻﺑﻦ ﻛﺜﻴﺮ