Translation is not possible.

የፍልስጤም ታሪክ

ምዕራፍ -2

እስራኤል ክፉ ፅንስ

ክፍል-5

[ተፃፈ-በአብዱልከሪም ሙሐመድ]

ፍልስጤም በእንግሊዝ ስር መዋል ከጀመረች በኋላ ውጥረት ነግሷል፤የሁለቱም ወገን እዚም እዚያም ሲጎሻሸም ቂም እንዳዘለ ቆይቷል፡፡ የሰላም አየር ተናፍቋል ይባስ ብሎ የዳኛውን ፊሽካ እንደሚጠብቁ የቦክስ ተጋጣሚዎች ፍጥጫው አይሏል፡፡

ለዚህም በፌብሯሪ 1936 የተከሰተው አጋጣሚ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡ ያፋህ ውስጥ በመንግስት ወጪ በሚሰሩ 3 ትምህርት ቤቶች ኮንትራክተር የነበረው አይሁዳዊ አንድም አረብ ሰራተኛ ለመቅጠር ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ፊት የተነፈጉት ሰራተኞች እሳት ለባሰው እሳት ጎርሰው በስራ ቦታው በመሰባሰብ አንድም አይሁዳዊ ወደዚያ ዝር እንዳይል አደረጉ፡፡

ከጥቂት ግዜያት በኋላ በኤፕሪል 15 አንድ አይሁድ ሲገደል ሌላኛው ክፉኛ ቆሰለ፡፡ አይሁዶች በአፀፋው አረብ ገበሬዎችን በቤታቸው ጨፈጨፏቸው፡፡ ይህ ክስተት ነው እንግዲህ የተርከፈከፈው ነዳጅ ላይ ክብሪት የለኮሰው፡፡ እዚም አዛም ፀብ እየተነሳ በሁለቱም ወገን ብዙ ሰው አለቀ፤ የእንግሊዝ ወታደሮች የሚወሰድ እርምጃ የሞት መጠን ሚዛኑ ወደ ፍልስጤማዊያን እንዲያጋድል አደረገው፡፡

ነገሮች ከድጡ ወደማጡ ሲሄዱ ምድሪቷ በደም ጨቀየች፡፡ የሀገሪቷ ዜጎች አድማና አመፅን በማወጅ ብሔራዊ ተቃውሞን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡በቡድን አየተደራጁ ሲንቀሳቀሱ ሌሎች ፍቃደኛ አረቦች ከምስራቅ ዮርዳኖስ፣ ሶሪያ፣ ሊባኖስ እና ኢራቅ ተቀላቀሏቸው፡፡

ይህ መሆኑ አመፁን ወደ ጦረኛ አብዮት አሳደገው፡፡ ድልድይ በማፈራረስ፣ የባቡር ሀዲዶችንና የነዳጅ ማስተላለፊያዎችን በማፈንዳት እንዲሁም ወሳኝ ቦታዎች ላይ ቦምብ በመጣል ቀውጢ አደረጉት፡፡

የፈረጠመ ክንድ ያላት እንግሊዝ የአየር ሀይሏንና ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን (መድፍ እና ሌሎችን) በመጠቀም አመፁን ለማዳፈን ብትሞክርም አልተሳካላትም፡፡ በዚህ ግዜ ብቸኛ አማራጭ ወደ ሆኑት ወደ ቀድሞ ወዳጆቿ ሮጠች፡፡

እነ ንጉስ ቢን ሳዑድ (አብዱልአዚዝ)፣ ንጉስ ጋዚ እና ልዑል አብዱሏህ ጥሪዋን በመቀበል በኦክቶበር 10 መከሩ፡፡ በዚህም ለፍልስጤማዊያን የሚከተለውን መልዕክት አስተላለፉ፡፡

‹‹በዚህ የፍልስጤም ሁኔታ እጅጉኑ አዝነናል፣ እናም እኛ የአረብ ንጉሶችና ልዑል አብዱሏህ ሰላማዊነት እንዲመለስ እና ደም መቃባት እንዲያበቃ ተስማምተናል፡፡ በአጋራችን በእንግሊዝ መንግስት በጥሩ ተነሳሽነት የታቀደውን ፍትህ ለማስፈፀም እኛም እናንተን ለመርዳት ጥረት እንደምናደርግ በመተማመን ነው፡፡››

የተደገሰላቸውን ያላወቁ የዋሆች ይህንን ጥሪ በመቀበል አመፁ እንዲቆም በማድረግና 2ሺህ የሚደርሱ ሰማዕታት ላይ ሰላት በመስገድ አብዮቱ ተጠናቀቀ፡፡

Send as a message
Share on my page
Share in the group