Translation is not possible.

#አማራ #ዋግኽምራ

" ሰው ሁሉ ግራ ተጋብቶ የሚበላውንም አጥቶ ነው ያለው፤ ታይቶም ተሰምቶ የማይታወቅ በጣም የሚዘገንን ድርቅ ነው ያጋጠመን  " - የዋግኽምራ ምሽሃ ቀበሌ ነዋሪ

በአማራ ክልል፣ ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ፤ ሰሀላ ሰየትም ወረዳ ውስጥ ስላለው አስከፊ የድርቅ ሁኔታ በተደጋጋሚ መነገሩ ይታወሳል።

በአካባቢው ስለሚገኙ ዜጎች ሁኔታ ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳይ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ መልዕክቶችን ማጋራቱም ይታወሳል።

አሁንም ችግሩ በከፋ ሁኔታ ላይ ሲሆን በርካታ ወገኖች በድርቁ ችግር ውስጥ ይገኛሉ። ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ እንስሳትም መኖ ፍለጋ ወደ አጎራባች ወረዳዎች ተሰደዋል።

በዚሁ አካባቢ ስላለው አስከፊ የድርቅ ሁኔታ ከሰሞኑን ቃላቸውን ለቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ የሰጡ ወገኖች " ቀጣይ ኑሯችን ተስፋም የለው " ብለዋል።

አርሶ አደር ደሴ ፈንቴ ፤ የምሸሃ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ባለፈው ክረምት በቀበሌው ምንም አይነት ዝናብ ባለመጣሉ እርሳቸውም ሆኑ ከብቶቻቸው የሚበሉት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በድርቁ ምክንያት የጎረቤቶቻቸው ህይወት እንዳለፈም የገለፁት አርሶ አደሩ ፤ የቤት እንስሳቶቻቸው በመሞታቸው ቀጣይ ኑሯቸው ተስፋ እንደሌለው ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የ01 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ነጋሽ ጎበዙ ፤ " 2015 ለ2016 ምንም አይነት ሳርም ሆነ ሌላ ነገር ያልበቀለበት ፤ ታይቶም ተሰምቶ የማይታወቅ በጣም የሚዘገንን ድርቅ ነው ያጋጠመን። ሰው ሁሉ ግራ ተጋብቶ የሚበላው አጥቶ እስሳቱንም ትቶ፣ ሰውም በየቦታው እየሞተ፣ እንስሳቱም እየሞቱ በጣም የከፋ ሁኔታ ላይ ነው ደርሰን ያለነው። በጣም በጣም አስከፊ ነው። " ብለዋል።

እሳቸው የነበራቸው በርካታ ከብቶች እና ፍየሎች በረሃብ ሞተውባቸው እንዳለቁ ተናግረው ፤ " የከብቱስ ይሁን እሳሳት ናቸውና እጅግ የሚያሳዝነው የሰዎች ህይወት እያለፈ መሆኑ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት እሳቸው ባሉበት አካባቢ 2 ህፃናት እና 3 አዛውንቶች በአጠቃላይ 5 ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል።

ከሰሞኑን በዋግኽምራ ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ከመንግስታዊና 18 ከሚደርሱ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጣ የባለሞያዎች ቡድን በአካል ተገኝቶ ጥናት ማድረጉ ተነግሯል።

በዚህም ጥናት በሰው እና እስሳት ሞት ላይ ዳሰሳ ተደርጓል።

ምንም እንኳን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ለድርቅ ተጎጂዎች በሚል የዕለት እርዳታ እንደላከ ቢያሳውቅም የዋግኽምራ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ድጋፉ በቂ እንዳልሆነ አሳውቋል።

ያለው ችግር የእንስሳት መኖ እጥረት፣ የሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እጥረት ...ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሆነ የገለፀው ፅ/ቤቱ " የክልሉ መንግስት 600 ኩንታል ስንዴ፣ ፌዴራል መንግስት 675 ኩንታል ስንዴ አቅርበዋል፣ ረጂ ድርጅቶች 42 ሚሊዮን ብር የሚሆን በካሽ የሚከፈል አቅርበዋል። አሁን ላይ ለአንድ ወር የሚሆን 25,834 አካባቢ ሰዎችን ሊያግዝ የሚችል ድጋፍ አግኝተናል ይህ ግን ካለው ችግር አንፃር በቂ አይደለም " ብሏል።

ተጨማሪ ድጋፍ ካልተደረገ ተጨማሪ ጥፋት ሊደርስ ይችላል ሲልም ፅ/ቤቱ መግለፁን ቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ ዘግቧል።

Via tikvahethiopia

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group