Translation is not possible.

ጋዛ ውስጥ በ1965 (እአአ) የተወለደው ሞሐመድ ዳይፍ አል-ማስሪ በቅጽል ስሙ “አቡ-ኻሊድ” ወይም “አል-ዳይፍ” የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የኢዝ አል-ቃሳም ብርጌድ መሪ ነው።

በፍልስጥኤማውያን ዘንድ “ዋነኛው አንቀሳቃሽ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ እስራኤላውያን ደግሞ “የሞት መልዕክተኛ” ወይም “ባለዘጠኝ ነፍሱ ተዋጊ” በሚል ይጠራል።

ሞሐመድ ዳይፍ ጋዛ ውስጥ ከሚገኘው እስላማዊ ዩኒቨርስቲ ባዮሎጂ አጥንቶ በዲግሪ የተመረቀ ሲሆን፣ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ለትወና እና ለቲያትር ባለው ፍቅር እንዲሁም የኪነ ጥበብ ቡድን በማቋቋሙ ይታወቃል።

ዳይፍ ሐማስ መመሥረቱ ሲገለጽ ቡድኑን የተቀላቀለው በሙሉ ልብ አልነበረም። በ1989 (እአአ) ለሐማስ ወታደራዊ ቡድን ይሠራል ተብሎ በእስራኤል ባለሥልጣናት ከተያዘ በኋላ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ ለ16 ወራት ታስሮ ነበር።

በእስር ላይ በቆየበት ጊዜም ዳይፍ ከዛካሪያ አል-ሾርባጊ እና ከሳላህ ሺሃዲህ ጋር በመሆን ከሐማስ የተለየ የእስራኤል ወታደሮችን የሚማርክ ቡድን ለመመሥረት ተስማማ። ይህ እንስቃሴ ነው እንግዲህ ጎልብቶ አል-ቃሳም ብርጌድ ለመሆን የቻለው።

ዳይፍ ከእስር ከተፈታ በኋላ የኢዝ አል-ቃሳም ብርጌድ ወታደራዊ ቅርጽ በመያዝ መንቀሳቀስ ጀመረ፣ ዳይፍም ከሌሎች የቃሳም መሪዎች ጋር በመሆን የቡድኑ ቀዳሚ መሥራች ለመሆን ቻለ። የደይፍ የሀማስ ተዋጊዎች ከጋዛ ተነስተው ወደ እስራኤል እንዲገቡ የሚያስችላቸውን የመሬት ውስጥ መተላለፊያ ዋሻን የቀየሰው እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሮኬቶችን በአንድ ጊዜ የመተኮስ ሃሳብን ካራመዱት መካከል አንዱ ነው።

ከሁሉም በላይ በእስራኤል ከሚቀርቡበት ከባባድ ክሶች መካከል የሐማስ ቦምቦችን ይሰራ የነበረውን የያህያ አያሽ ግድያን ለመበቀል እንደ አውሮፓውያኑ 1996 መጀመሪያ ላይ 50 እስራኤላውያን የተገደሉባቸውን የአውቶብስ የቦምብ ጥቃቶች፣ እንዲሁም በ1990ዎቹ አጋማሽ ተማርከው የተገደሉ ሦስት እስራኤላውያን ጉዳይ ይጠቀሳሉ።

እስራኤል ዳይፍን በ2000 ላይ ይዛ አስራው የነበረ ቢሆንም፣ ሁለተኛው የፍልስጥኤማውያን አመጽ ሲቀሰቀስ ለማምለጥ ችሏል። ከዚያ በኋላም የት እንዳለ አይታወቅም።

አስካሁን የሚታወቁ የዳይፍ ሦስት ፎቶዎች አሉ። አንደኛው በጣም ያረጀ፣ ሁለተኛው ጭምብል አድርጎ እና ሦስተኛው ጥላውን የሚያሳዩ ናቸው።

ዳይፍ በጣም አደገኛ የሚባል የመግደል ሙከራ የተደረገበት በ2002 (እአአ) ነበር። በጥቃቱ ዳይፍ ተዓምር በሚባል ሁኔታ ቢተርፍም አንድ ዐይኑን አጥቷል። አስራኤል ግን በጥቃቱ በተጨማሪ አንድ እጁን እና እግሩን ማታቱን እንዲሁም በተደጋጋሚ በተፈጸሙበት የግድያ ሙከራዎች ምክንያት የመናገር ችግር ገጥሞታል ትላለች።

በአውሮፓውያኑ 2014 የእስራኤል ሠራዊት ለ50 ቀናት የቆየ ጥቃትን በጋዛ ሰርጥ ላይ ባካሄደበት ጊዜ ዳይፍን ለመግደል ሳይችል ቢቀርም፣ ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን ገድሏል።

የሐማሱ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ዳይፍ የሚለውን ስም የወሰደው “እንግዳ” ከሚለው የአረብኛ ቃል ነው። ምክንያቱም የእስራኤልን ግድያ ለማምለጥ አንድ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ስለማይቆይ እና በየምሽቱ ለማደሪያነት የሚጠቀምብትን ስፍራ ስለሚቀያይር ነው።

ፈጣን እና ተአማኒ ለሆነ መረጃ #follow ያድርጉ

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group