UMMA TOKEN INVESTOR

Followings
0
No followings

🏝 አስደናቂው የሰልማን አልፋሪሲ 🏝

. የህይወት ታሪክ ክፍል~አንድ

~~~~~~~~~~~~~

📚 በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ በጣም ሩህሩህ በሆነው እጀምራለሁ

📚 ኢማሙ ሙስሊም ከአብደላህ ኢብኑ መስዑድ ረዲያሏሁ ዐንሁ በዘገቡት ሀዲስ ነብያችን ﷺ እንዲህ ብለዋል:-

📚 ما من نبي بعثه الله في أمة قبلي إلا كان له من أمته حواريون وأصحاب، يأخذون بسنته ويقتدون بأمره، ثم إنها تخلف من بعدهم خلوف يقولون ما لا يفعلون، ويفعلون ما لا يؤمرون، فمن جاهدهم بيده؛ فهو مؤمن، ومن جاهدهم بلسانه؛ فهو مؤمن، ومن جاهدهم بقلبه؛ فهو مؤمن، وليس وراء ذلك من الإيمان حبة خردل

📚 “የእርሱን ፈለግ የሚይዙና ትዕዛዙን የሚከተሉ ረዳቶች እና ባልደረቦችን ከህዝቦቹ አድርጎለት እንጂ አሏህ አንድንም ነብይ ከእኔ በፊት አልላከም፤ ከዚያም ከእርሱ በኋላ የማይተገብሩትን የሚናገሩ ያልታዘዙትን የሚሰሩ ይተካሉ ፡፡ (እነኚህን ሰዎች) በእጁ የታገላቸው ሙእሚን(አማኝ) ነው፤ በምላሱም የታገላቸው ሙእሚን ነው፤ ከዚህ በኋላ የሰናፍጭ ፍሬ ያህል እንኳ ኢማን እምነት የለም”

👉አላህ በተለያዩ የቁርኣን አንቀፆች ነብዩም ﷺ በብዙ የሃዲስ ጥቅሶች ሰሐቦችን ያወድሷቸዋል ። ለኛም ሞዴል የተደረጉ ለእስልምናም ትልልቅ ጀብዶችን የሰሩ ትልልቅ መሰዋእቶችንም የከፈሉ በሁሉም ነገራቸው አስተማሪ የሆኑ ባህሪያቸውና ስነ_ምግባራቸውና ስብዕናቸው ሁሉ ከእነሱ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ ትምህርትና ትልቅ ተምሳሌትም ነው።

ከነዚያ ከነቢዩ ሙሐመድ ﷺባልደረቦች እስልምና ውስጥ ትልቅ ትውስታ ካላቸውና ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ስብዕናዎች አንዱ የሆነው የሰልማን አል ፋሪሲ የህይወት ታሪክ ላወጋቹ ወድጃለው ።

📝ሰልማን አልፋሪሲ ማለት:- የትውልድ ሀገሩ ድሮ ፐርሺያ አሁን ኢራን ተብላ ከምትጠራው ሀገር ነበር።

ከሰልማን አልፋሪሲ አስደናቂ ታሪኮች ውስጥ በዕድሜ ጠገብትነቱ ይጠቀሳል አንድ መቶ ሃያ(120)ዓመታት በህይወት እንደኖረ የታሪክ ምሁራን በድርሳኖቻቸው አውስተዋል ።

ሰልማን አልፋሪሲ ረዲየላሁ ዐንሁ ከሀገሩ ሲነሳ እሳት አምላኪ ከነበሩ ሰዎች መንደር ውስጥ የወጣ ታላቅ ሰው ነበር ።

ከሃገሩም የወጣበት ምክንያት እውነትን ፍለጋ ነው።

እውነትንም ፍለጋ ከሀገር ወደ ሀገር መሰደድ እና ከፍተኛ እንግልትም ደርሶበታል ።

ይህም ሲሆን ግን እውነትን ከመፈለግ በፍፁም አልታከተም ።

እውነትን ለማግኘት ከነበረው ትልቅ የሆነ ሞራልና ጠንካራ የሆነ ወኔ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡት ሁሉ ትልቅ የሆነ ተምሳሌት ነው ።

◉ ሰልማን አልፋሪሲ ከነብዩ ባልደረቦች ውሰጥ በግንባር ቀደምትነት ይወሳል ::

ከዚህ በፊት ሰለነበሩት መፅሐፍቶች እውቀት የነበረውና በእስልምናም ላይ ትልቅ አዋቂ የሆነ ሰው ነው ::

ከሰልማን ባልደረቦች ከነበሩት ውስጥ አንዱ ሙአዝ ኢብኑ ጀበል ረዲያሏሁ ዐንሁ የተባለው ሶሃባ ነብዩﷺ እስልምናን እንዲያሰተምር ወደ የመን ከላኩዋቸው ሳሃባዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ሙአዝም ረዲያሏሁ ዐንሁ ሊሞት ሲል ባልደረቦቹ <<ሙአዝ ሆይ እስቲ ምከረን ኑዛዜን ስጠን>> አሉት ።

እሱም እንዲህ ሲል ምክሩን ጀመረላቸው <<እውቀትና ዕምነት እቦታቸው ላይ ናቸው የፈለጋቸውማ ያገኛቸዋል የፈለጋቸው ይደርስባቸዋል እውነታን የፈለገ እውቀትን የፈለገ ያገኘዋል አያጣውም>> ብሎ ከመከራቸው በኋላ እውቀትን ከእነዚህ አራት ሰዎች ተማሩ ብሎ አብደሏህ ኢብኑ መሰኡድን አቡ ደርዳን አብደላ ኢብኑ ሰላምን ሰልማን አልፋሪሲን ረዲየላሁ ዐንሁማ ጠቅሶ ከእነዚህ እውቀትን ተማሩ ብሎ ኑዛዜውን አስተላለፈላቸው።

◉ ሰልማን አል ፋሪሲ እስልምናን የተቀበለው ነብዩ ﷺ ከመካ ወደ መዲና ከተሰደዱ በኋላ ነው።

◉ ሰልማን አልፋሪሲ የነብዩን መላክ እሳቸው ከመላካቸው በፊት ያውቅ ነበር ።

ከዚያ በፊት የነበሩት የመፅሃፍት አዋቂዎች አንብበው በነገሩት መሰረት ስለሚመጣው ነብይ እነሱ ዘንድ የነበረውን ትንቢት ነግረውት ስለ ነበር በጉጉት ይጠባበቅ ነበር።

👉💫ከተነገረው ትንቢት ውስጥ ይህ ነብይ ከየት እንደሚወጣና ምን አይነት የነብይነት ምልክት እንዳለው በቂ መረጃ ሰለ ነበረው ይህንን ምልክት ይዞ ይጠባበቅ ጀመር።

◉ ነገር ግን ከብዙ እንግልትና ችግር በኋላ አላህ አመቻችቶለት በስተመጨረሻ ላይ ሲያስበው ወደ ነበረው ቦታ አደረሰው የሚመኘውንም ነገር አገኘ።

◉ ነገር ግን እውነትን ለመፈለግ ትልቅ የሆነ ትግልን ያደረገ ትልቅ የሆነ መሰዋአትንም የከፈለ ታሪካዊ ጀብድንም የፈፀመ ለሌሎችም እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ ተምሳሌት የሚሆን ታላቅ ሰው ሆነ።

◉ ታሪኩንም ለመዳሰስ የተፈለገው ከእርሱ ህይወት ትምህርትን እንድንወስድና እኛም እውነትን በመፈለግ ላይ መታከት እንደሌለብን እንድንረዳ ነው።

◉ ነብዩም ﷺ ሰልማንን እስልምናን ከተቀበለ በኋላ የህይወት ታሪኩን ሲነግራቸው እስቲ ቁምና ለባልደረቦችህ ንገራቸው አሉት።

ይህም ሌሎች ሰዎች ከሰልማን ቁም ነገርን እንዲማሩ ፈልገው ነው።

◉ ሰልማን እስልምናን ከተቀበለ በኋላ እስልምናን ተምሮ ትልቅ አስተማሪም ለመሆን በቅቷል ።

በእስልምና ታሪክ ከተደረጉ ዘመቻዎቻ ውሰጥ የበድርና ኡሑድ ዘመቻዎች በባርነት ምክንያት ሳይካፈል ቢቀርም ከዚያ በኋላ የነበሩ ዘመቻዎችን ግን ሙሉ በሙሉ ተሳትፏል።

በኡመር ኢብኑ አል ኸጣብ ረዲየላሁ ዐንሁ ዘመን (መዳኢን) በተባለ ሀገርም አሰተዳዳሪ ሆኖ አገልግሏል ።

ከነቢዩም ﷺ መሞት በኋላ እስልምና ሲስፋፋ ትልቅ አስተዋፆ አድርጓል። የሞተውም በ36ኛው ዓ.ሂ. በኡስማን ዘመነ መንግስት (ኺላፋነት) ወቅት ነው በሚል የታሪክ ሙሁራን ዘግበዋል ።

📝ኢማሙ አህመድ የተባሉት የኢስላም ሊቅ ሙስነድ በሚባለው ኪታባቸው(መፅሀፋቸው ላይ) እንደዘገቡት ፦

አብደላህ ኢብኑ አባስ ታሪኩን እንዲህ ሲል ነገረኝ ብሎ ይጀምራል።

👇 በአላህ ፍቃድ ክፍል ሁለት ይቀጥላል👇

✏️አቡ ሙጃሂድ አብዱረህማን

Send as a message
Share on my page
Share in the group
Hasen Abdrezak Сhanged his profile picture
1 year
Translation is not possible.

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group