የምርኮ ገንዘብ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
8፥1 ከአንፋል ይጠይቁሃል፡፡ በል፦ «አንፋል የአሏህ እና የመልእክተኛው ናቸው፡፡» يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْأَنفَالِ ۖ قُلِ الْأَنفَالُ لِلَّهِ وَالرَّسُولِ
የግጭት አዙሪት እና የጭቅጭቅ ቀለበት አባዜ የተጠናወታቸው ሚሽነሪዎች "ቁርኣን ዝረፉ ይላል" በማለት መጥኔ የሌለው ሥርዋጽ ሲለቁ እያየን ነው፥ የመካከለኛው ምሥራቅ ትኩሳት ተስታኮ ለማሳጣት ሾርኔ መሆኑ ነው። "ጅብ በቀደደው ውሻ ይገባል" ነውና ነገሩ መስመር የሳተ አስተሳሰብ ቢሆንም ጥሩ የውይይት ማሳለጫ ነው፥ ከከርሞ ዘንድሮ ለያዥ ለገናዥ በማያመች መልኩ ቅሌቱ ቢያገረሽባቸውም እኛ ደግሞ "ከፋህም ከረፋህም" ሳንል መልስ እንሰጣለን።
"ነፈል" نَفَل የሚለው ቃል"ነፈለ" نَفَلَ ማለትም "ማረከ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ምርኮ" ማለት ነው፥ የነፈል ብዙ ቁጥር ደግሞ "አንፋል" أَنفَال ሲሆን "ምርኮዎች" ማለት ነው፦
8፥1 ከአንፋል ይጠይቁሃል፡፡ በል፦ «አንፋል የአሏህ እና የመልእክተኛው ናቸው፡፡» يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْأَنفَالِ ۖ قُلِ الْأَنفَالُ لِلَّهِ وَالرَّسُولِ
እዚህ አንቀጽ ላይ በዐማርኛ ትርጉም ላይ "የጦር ዘረፋ" "የዘረፋ ገንዘብ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "አል አንፋል" الْأَنفَال ሲሆን በቀላሉ ከጦነት በኃላ የሚገኙ "ምርኮዎች" ናቸው፥ 8ኛ ሡራህ እራሱ ስሙ "ሡረቱል አንፋል" سُورَة الْأَنفَال ነው። ይህም ምርኮ አንድ አምስተኛው ለአሏህ፣ ለመልእክተኛው፣ ለዝምድና ባለቤቶች፣ ለየቲሞች፣ ለምስኪኖች፣ ለመንገደኛ የተገባ ነው፦
8፥41 ከማንኛውም የምርኮ ገንዘብ የዘረፋችሁትም አንድ አምስተኛው ለአሏህ እና ለመልእክተኛው፣ የዝምድና ባለቤቶችም፣ ለየቲሞችም፣ ለምስኪኖችም፣ ለመንገደኛም የተገባ መኾኑን ዕውቁ። وَاعْلَمُوا أَنَّمَا غَنِمْتُم مِّن شَيْءٍ فَأَنَّ لِلَّهِ خُمُسَهُ وَلِلرَّسُولِ وَلِذِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينِ وَابْنِ السَّبِيلِ
በቁርኣን ስለ አንፋል እዚህ ድረስ አጥለን እና አጠንፍፈን ከተረዳን ዘንዳ መጅ እና ወፍጮ ይዘን ስለ ምርኮ በባይብል የተነገሩት በቅጡ አድቅቀን እናያለን። ነቢዩ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከነገሥታቱ የዘረፈውን ለሳሌም ንጉሥ ለመልከ ጼዴቅ ሰጥቶታል፦
ዕብራውያን 7፥4 የአባቶች አለቃ አብርሃም "ከዘረፋው" የሚሻለውን አስራት የሰጠው ይህ ሰው እንዴት ትልቅ እንደ ነበረ እስኪ ተመልከቱ።
"ከዘረፋው" የሚለው ይሰመርበት! አብርሃም በጦርነት ምርኮን ስለዘረፈ ሌባ ነውን? መዝረፉስ ሌብነት ነውን? ጉድ ፈላ፥ ይህ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። የያዕቆብ ልጆች እኅታቸው ዲና ስለተደፈረች ደፋሪዎችን ገድለው በከተማይቱ ያሉትን በጎቻቸውን፣ ላሞቻቸውን፣ አህዮቻቸውን፣ በውጭም ያለው፣ ሀብታቸውን ሁሉ፣ ሕፃናቶቻቸውን፣ ሴቶቻቸውንም እና በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ፦
ዘፍጥረት 34፥27-29 የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን "ዘረፉ"፤ በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ። ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ "ዘረፉ"።
"ዘረፉ" የሚለው ይሰመርበት! ይህንን ስታነቡ ሰኔ እና ሰኞ ይሆንባቸዋል። በዚህ ቢቆም ጥሩ ነበር፥ እስራኤላውያንም ከግብፅ ሲወጡ የግብፅ ንብረት በዝብዘው ነበር። ይህንን ያደረጉት ከተማይቱን በማቃጠል ነው፥ ይህንን ያዘዛቸው የእስራኤል አምላክ እንደሆነ ባይብሉ ይናገራል፦
ዘጸአት 3፥22 ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር ዕቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም "ትበዘብዛላች"።
ዘጸአት 12:36 እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን "በዘበዙ"።
"ትበዘብዛላች" የሚለው መጻኢ ግሥ እና "በዘበዙ" የሚለው አላፊ ግሥ ይሰመርበት! በትእዛዙ መሠረት በመንገድ ላይም ያደረጉት ይህንን ተግባር ነው ፦
ዘኍልቍ 31፥9-11 የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን "ማረኩ"፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ "በዘበዙ"። የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። "የሰውን እና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ"።
ዘኍልቍ 31፥53 ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ "ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ"።
ኢያሱ 8፥27 ነገር ግን ያህዌህ ኢያሱን እንዳዘዘው ቃል የዚያችን ከተማ ከብት እና ምርኮ እስራኤል ለራሳቸው "ዘረፉ"።
ኢያሱ 11:14 የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው "ዘረፉ"።
ስለ ዘረፋ በባይብል ልቀጥል ብል ቦታ አይበቃኝም፥ አንባቢንም ማሰልቸት ነው። መቼም ሚሽነሪዎች የኢሥላም ትምህርት ጥንብ እኩሱን ቢወጣ እና ዶግ አመድ ቢሆንላቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ ነው፥ ይህ ጡዘቱ ጣራ የነካና ዙሪያ ገባ ምኞች ስለማይሳካ በቁጭ ይሙቱ! ከእነርሱ ቅንነት የተሞላው ትምህርት መጠበቅ ማለት ከጅብ አፍ ላይ ሥጋ እንደመጠበቅ ነው። እነርሱ የሚሰጡት ትችት እኛ ሙሥሊሞችን የሚያፍረከርክ ሳይሆን ከእለት ወደ እለት የሚያጀግን ነው፥ ለማንኛውም የተነሳውን ትችት አብጠርጥረን እና አንጠርጥረን መልስ ሰተናል። አሏህ ለእነርሱ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
ወሠላሙ ዐለይኩም