Translation is not possible.

የኤርዶጋንና የናታንያሆ ስምምነት እስከየት?

ለአመታት የዘለቀውን የቃላት ጦርነት ጋብ በማድረግ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋንና የእስራኤል ጠ/ሚ ናታንያሆ ኒዎርክ በተካሔደው የተመድ ስብሰባ ላይ መስከረም 8/2016 በግል ተገናኝተው ነበር።በወቅቱ ናታንያሆ የፍልስጤምን ህልውና የሻረ አዲስ ካርታ ይዘው ታይተዋል።እስራኤል «መሪ ተዋናይ» የምትሆንበት የመካከለኛው ምስራቅ የንግድ ጥምረትን ለማመላከት መድረክ ላይ ወጥተው ያቀረቡትን ንግግር ምኞት መስሎ ቢታይባቸውም ሐማስን ከጥርስ መንከስም ባሻገር እርምጃ ይወስድ ዘንድ የገፋፋው ይመስላል።

በመስከረም 10/2016 ኤርዶዋን እስራኤልና ቱርክ የሐይል ማመንጫ ስርጭትን እስከ አውሮፓ ለማዝለቅ የቁፋሮ ስራን ለመጀመር መስማማታቸውን መግለጻቸውን የቱርክ ሚዲያዎች አሳወቁ።ኤርዶጋን የእስራኤልና የቱርክ የንግድ ትብብር 9.5 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ቢሆንም አገራቱ እስከ 15 ቢሊየን ዶላር ሊያሳድጉት መስማማታቸውን አሳወቁ።ከማን መሬት ላይ ነው ለሐይል ማመንጫ የተፈጥሮ ጋዝ ተቆፍሮ የሚወጣው? እስራኤል በሐይል በያዘቻቸው ግዛቶች ወይስ ከጋዛ? የቱርክና የእስራኤል ስምምነት ጥልቅ ማብራሪያን ይሻል።

በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ስር ከነበረቸው አዘርባጃን ተነስቶ እስከ ቱርክ የሚዘልቅ የ1768 ኪሎ ሜትር (1099 ማይል) ትቦ ለነዳጅ ዘይት ማመላለሻነት ተዘርግቷል።ለቱርክና ለሌሎች አገራት የሽያጭ ፍጆታ ይሆን ዘንድ አንካራና ባኩ ስምምነት አላቸው።ከአዘርባጃን ለእስራኤል የተሸጠው አንድ ሚሊዮን በርሜል የነዳጅ ዘይት ድፍድፍ ሰይሃን በሚባለው የቱርክ ወደብ ተጭኖ ወደ እስራኤል ማቅናቱን የብሉምበርግ ዘገባን ዋቢ አድርገው የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል። የአዘርባጃን ሚዲያዎችም ነዳጁ በመርከብ ተጭኖ ሐማስ ወዳጠቃው አሽኬሎት ወደብ ሳይሆን ኤይለት ወደብ ማቅናቱን አረጋግጠዋል።

ላይ ከሰፈሩት ሁለት መረጃዎች መገንዘብ የሚቻለው አገራት በመገናኛ ብዙሗን የሚሽከረከር «ትርክትን» ቢፈጥሩም የአገራቸውን ጥቅም በማስከበር ደረጃ የሚወስዱት አቋም ለየቅል መሆኑን ነው።የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ኢስላማዊ እሴቶችን በማጉላትና ኢስላማዊ ተቋማት በመላው አለም በመገንባቱ ረገድ በላፉት አስር አመታት ያሳዩት እምርታዊ ጥረት በሙስሊም አገራት ጎዳናዎች ላይ ተመስጋኝ አድርጓቸዋል።በተለያዩ አገራት ያለው ሙስሊም ዜጋ የሚፈልገውን ነገር በመናገር መነቃቃትን ይፈጥራሉ። የአገራቸውን የዲፕሎማሲ አቋምና የሚያራምዱት ፖሊሲ ግን በተግባር ደረጃ የተለየ ነው።

ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሳኡዲ አረቢያን፣ኳታርን፣ዮርዳኖስን፣ግብጽን፣ሶሪያያን፣ሊባኖስን፣ኢራንና ሌሎችን አገራት መቃኘት ይቻላል።ቀጣናው ውስጥ ቀውስ ነግሶ የጽዮናዊው የጦር ሐይል ተጠቃሚ እንዳይሆንና ቀውሱ ውስን ቦታ ብቻ እንዲቆይ ማድረጋቸው ገንቢ ነው።ግን ብሔራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው እንደማይሰጡ አሳይተዋል።ለምሳሌ ኢራን የሺዓ አገር ናት።የሊባኖሱ ሒዝቡላህና የየመኖቹ የሑቲ አማጽያን ሺዓዎች ናቸው።ሒዝቡላህና ሑቲ በኢራን ይረዳሉ። ሒዝቡላህና ሑቲ በተግባርም ይሁን በቃላት ጦርነት ከሐማስ ጎን መቆማቸውን አሳይተዋል። ይህ ቀደም ሲል የኢራን ግዛት የነበረችው፣ቋንቋንና ባህልን ከኢራን ጋር የምትጋራዋን ሺዓዋን አዘርባጃን አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይትን ለእስራኤል ከመሸጥ አላገዳትም።ቴላቪቭና ባኩ በዲፕሎማሲ ወላንሳ ላይ ሲንፈላሰሱ ቴህራን ባደባባይ አፍንጫዋን ብትነፋም ባኩ ቢያንስ በቴህራንና በቴላቪቭ መካከል ያለች መልእክተኛ ልትሆን ትችላለች ብሎ መገመት ይቻላል።

የአገራት ዲፕሎማሲያዊ አቋምና የሚፈጥሩትን ትርክት ለይቶ ማየቱ የሐሳብ ብግነትን በመቀነሱ ረገድ ይጠቅማል።ከእስራኤል ጋር የአረብ አገራት ሊያደርጉት የነበረውን መዋእለ-ነዋይን መሰረት ያድረገውን የትብብር ግንኙነት ያጤነው ሐማስ «ፍልስጤምን» መርሳት የለባችሁም የሚል ማስጠንቀቂያ ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ላከ። እስራኤል በቴክኖሎጂ ያጠረቸውን አጥር ጥሶ ጥቃት አደረሰ።እስራኤል የአጸፋ ምላሿን ሰጠች። የእስራኤል ምላሽ «እራስን ከመከላከል» በላይ ዘልጎ በዘር ማጥፋት አስኮነናት። ኤርዶጋን ሐማስን አሸባሪ ሳይሆን «የነጻነት ታጋይ» ነው ሲሉ ተናገሩ።እስራኤልን ደግሞ «አሸባሪ» ሲሉ ኮነኑ።

ኤርዶጋን የአገራቸውን ህዝብ አነቃቅተው በታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መገኘታቸው የለመለመው ገጽታቸው መለምለሙ ይቀጥል ዘንድ የተርከፈከፈ ውሃ ሆኗል።ቆጣ ብለው ስለፍልስጤም ነጻነት መናገራቸው ምስጉንነታቸውን አስቀጥሏል።ከናታንያሆ ጋር የነበራቸው እጅ መጨባበጥና ያደረጉት የኢኮኖሚ ስምምነት ከአር-እስተ ዜናነት ወርዷል። ወይም በአጭር የእሳቤ ምህዋር ውስጥ የተሽከረከረ አጋጣሚ በመሆኑ ተረስቷል።

ቱርክ ከእስራኤል ጋር የነበራቸው የቁፋሮ ስምምነት ይጸና ይሆን? ስምምነቱ ተሰናክሏልን ወይስ ዘግይቷል? ይህ በሒደት የሚታይ ቢሆንም አሁን እየታየ ያለው በምድሪቱ ላይ የሚንቆረቆር የፍልስጤማውያን ደም ነው።ከፍራሽ መካከል የሚለቀም የፍልስጤማውያን አስክሬና የሰማእታት ቤተሰቦች ጥንካሬ ነው እየታየ ያለው።

ልብ ያለው ልብ ይበል!

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group