Translation is not possible.

«እማ»

--------------------------

አውጥቼ አውርጄ እርእስ አልመርጥም፡

ፍቅሬን በምን ቋንቋ እያልኩኝ አልቀብጥም፡

ብቻ ግን ፃፍኩላት ያው ስራዬም አይደል?

ብራናዬ አጥሮብኝ ካላነሰኝ ፊደል፡

ስለ እሷ የማውቀውን ታምርና ገድል፡

ከልኳ ጫፍ ሳላልፍ ከክብሯ ሳላጎድል፡

እጽፋለሁ እኔ ያየሁትን እውነት፡

ልጇ ሆኘ ለርሷ እማ በሚል እምነት፡

------------------------------

የሴቶች የበላይ የፍቅር አሻራ፡

ገፀ-በረከቴ የተስፋ ቢሻራ፡

እናት በሚል ስምሽ አለምን የቃኘሽ፡

የፍቅር ውብ ቅኔ ሁሉም የተመኘሽ፡

እናት እና ፍቅር አንድ አይነቶች ናቸው፡

በሶስት ፊደላት ሁሉም ያወቃቸው፡

ለሁሉም ፍጥረታት አዛኝ ነው ልባቸው፡

-----------እማማዬ------------

በገረጣው ፊቷ ተፅፏል ታሪኳ፡

ያደፈ ቢመስልም ተውቦ አለ መልኳ፡

ረቂቅ ነው ቅኔው የናትነት ልኳ፡

ሳቄ ደስታዋ ነው ሀዘኔም ሀዘኗ፡

የኔ ልጂነት ነው የእማዬ ሚዛኗ፡

ጧትም ማታም ቢሆን «ልጄ»ነው ልሳኗ፡

ጤናዬ ጤናዋ ህመሜ ህመሟ፡

ለልጇ መኖር ነው የህይወት ቅመሟ፡

--------------------------------

          «እማ»

         --------

ተቆጥታኝ እንኳን አይታኝ ትራራለች፡

ውስጧን ቢከፋውም ለእኔ ትስቃለች፡

ብዙ ውጣውረድ ብዙ ፈተና አልፋ፡

ወዝና ቀለሟን ከፊቴ ላይ ፅፋ፡

እኔ እንድቃናላት እርሷ ጎንበስ ያለች፡

በልጅነት ዕድሜ ገና ለጋ ሳለች፡

ምኑንም ሳታውቀው ወልዳ ያሳደገች፡

የእርሷን ህይወት ትታ ለኔ ነፍስ የኖረች፡

--------------------------------

እድሜዋን በሙሉ ለደስታዬ ኖራ፡

ሀሴት የምትሰጠኝ ስሜን ስትጠራ፡

ለትንሽ ጊዜ እንኳን ከፊቷ ስሰወር፡

ፈጥኖ የሚመታ የልቧ መዘወር፡

ዘመን የማይፈታት እንኳን ትንሽ ቀናት፡

የደግነት አርማ ልዩ ነች የኔ እናት፡

-----------------------------

ምናብ መስላ፤

ግን እንደ ሰው በእውን ያለች፡

በእዝነቷ ጥልቀት፤

በጥበቧ ድምቀት ህልም መስላ የተሳለች፡

እማ ብዬ.....፤

በፍቅር ቃል በልቤ ላይ የደረስኳት፡

በቃሌ ላይ ሳልታጠፍ፤

የዘወትር ትዝታዬ በምናቤ የቀረፅኳት፡

እጂግ በጣም የምወዳት፤

የፍቅር መምህሬ ከራስ በላይ የማፈቅራት፡

እናቴ ነች በጥበቡ ፤

አምላካችን ንግሥት አርጎ የፈጠራት፡

በእውን አይኔ ስዬ፤

እያስታወስኩ እስከማያት የታመነች፡

እስከዛው ግን፤

በልቤ ያለች የልቦለድ ድርሰቴ ነች፡

----------እማማማዬ----------          

ላረግሽልኝ ሁሉ አልችልም ልክስሽ፡

ግና ቃል አለብኝ ሁሌም ላስታውስሽ፡

እንደ ልጅነቴ ልጦርሽ ባልችልም፡

ልቤ ላይ ነው ቀብርሽ ለምን አይባልም፡ በጀነት ሀገር ላይ ለማገኘት ያብቃኝ፡

በደማቅ ፈገግታች በሀሴት እንድቃኝ፡

     ----------እማማዬ------------

በጀነት እንዳይሽ አላህ እኔን ይርዳኝ፡

ፊት ለፊትሽ ሆኘ በፈገግታሽ ልዳኝ፡

አሏህ ይዘንልሽ ውብ አዳራሽ ሰቶ፡

ጀነት ያገናኘን ፊትሽን ልየው ፈክቶ፡

--------------------------------

የእድገቴ መሰረት የነገ አላማዬ፡

አሁን ላለኝ እውነት አንች ነሽ ማማዬ፡

ሰላም ላንች ይሁን ውበቴ እማማዬ፡

--------------------------

       በኑረዲን አል አረቢ

-----------------------------

t.me/nuredinal_arebi

t.me/nuredinal_arebi           

Send as a message
Share on my page
Share in the group