Translation is not possible.

#የተኩላ ነፃ አውጪ

እረኛው ፍየሎቹን ወደ ማደሪያ በረታቸው አስገብቶ ሁሉንም በሮች ዘጋቸው። ረሃብ

የጠናባቸው ተኩላዎች ምሽቱን ተገን አድርገው ከፍየሎቹ በረት ዙሪያ አንዣበቡ። ሁሉም

በሮች ተቆልፈዋል። የፍየል እግር መጎተቻ ቀዳዳ እንኳ የለም። ተኩላዎቹ የተስፋ መቁረጥ

ስሜት አጠላባቸው። አንድ ሴራ ሴራ ሸረቡ። ፍየሎቹን ከታጠሩበት በረት ነፃ ለማውጣት

የሚያስችል ሴራ። እቅዱን በጥንቃቄ ነደፉ። ከበረቱ ጎን ካለው የእረኛው ቤት ዙሪያ

የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሔድ ወሰኑ። ፍየሎቹ ነፃነታቸውን ይቀዳጁ ዘንድ ድምፃቸውን ከፍ

አድርገው ለማሰማት ተስማሙ።

.

.

.

.

" ነፃነት ለፍየሎች ! ... ፍየሎች ለዘመናት የተነፈጉት ተፈጥሯዊ መብታቸው ይከበር ! ...

ሌሎች የተጎናፀፉት ነፃነት ለፍየሎችም ይገባቸዋል! ..." የሚሉ መፈክሮች ከተኩላዎች

አንደበት ተስተጋባ። በበረቱ ዙሪያ የተካሔደው የተቃውሞ ሰልፍ ረዘመ። የእረኛው ቤት

በተኩላዎች አስገምጋሚ ድምፅ ተነቃነቀ። ፍየሎቹ የተቃውሞውን ድምፅ በትኩረት

እየተከታተሉ ነው። ለነፃነታቸው የሚሟገት ወገን በማግኘታቸው በደስታ ሰክረዋል።

መብታቸውን ለማስከበር የሚዋደቅ አጋር በመኖሩ ጮቤ ረግጠዋል። የተቃውሞ ሰልፉን

ባስተባበረው አካል ልበ ቀናነት አለቅጥ ተማርከዋል። ደመ ነፍሳቸው ድንገት ገነፈለ።

ከተቃውሞው ሰልፍ መሐል መቀላቀል ቋመጡ። የበረቱን ግድግዳዎች በቀንዶቻቸው

መንደል ጀመሩ። በሮቹን ሰባበሯቸው። ነፃ ወጡ። ተቃውሞውንም ተቀላቀሉ። መፈክራቸውን

እያሰሙ ጉዞ ጀመሩ። እረኛው ፍየሎቹን እየተጣራ ሊመልሳቸው ቢሞክርም ጆሮ ዳባ ልበስ

አሉት። ነፃነት ባጎናፀፏቸው ተኩላዎች ታጅበው ሸመጠጡ። ከከተማው ራቁ። የተኩላዎች

መዋያ ከሆነ ጭው ያለ ሜዳ ላይ ደረሱ።

.

.

.

.

አሁን ጠባቂና ተመልካች በሌለበት የምድር ገፅ ላይ ይገኛሉ። የመፈክሩም የአገልግሎት

ዘመን ተጠናቋል። ህልውናው አክትሟል። ያቺ ሌሊት ነፃ ለወጡት ፍየሎች ጥቁር ሌሊት

ሆነች። በተቃራኒው ለተኩላዎቹ ወርቃማ ምሽት። የተስፋ ዳቦ በሻይ ሲያምጓቸው ከነበሩት

ተኩላዎች መንጋጋ ውስጥ ያለ ተስፋ የሚገቡባት ቅፅበት ቀረበች። ነፃ ወጪና ነፃ አውጪ

ተፋጠጡ። የነፃ አውጪዎቹ ጭምብል ተገለጠ። ትክክለኛ ማንነታቸው ገጠጠ። የነፃ

አውጪዎቹ የምግብ ፍላጎት ጣሪያ ነካ። ከዚያማ የነበረው ሁሉ እንዳልነበር ሆነ።

.

.

.

.

በፍየሎቹ ተስፋ ያልቆረጠው እረኛ በቀጣዩ ቀን ፍየሎቹን ፍለጋ ገባ። ፋናዎቻቸውን ተከትሎ

እያሰሰ ሳለ <<ነፃነት የተጎናፀፉ>> ፍየሎቹን አገኘ። ግና በደም የተጨማለቁ

አጥንቶቻቸውን እንጂ እነርሱን አላገኘም። በቦታው የስጋ ቁርጥራጮች እንጂ ፍየሎቹ

የሉም።

★★★ ★★★ ★★★

ሴቶች <<ለዘመናት የተነፈጉትን ነፃነት>> ለማጎናፀፍ በሚል በዓለም መድረክ ላይ

ተቃውሞ የሚያሰሙ አንዳንድ <<ለምድ አጥላቂ ተኩላዎች>> ህልማቸው ለሴቶች ነፃነትን

ማጎናፀፍ ሳይሆን እነርሱ በሴቶች ያሻቸውን <<ነፃነት>> ለመጎናፀፍ ነው።

በነፃነት ስም ሴቶችን ህያው አሻንጉሊት (Living doll) ለማድረግ ነው ..

የመብትሽ ተመጋች የተኩላ ነፃ አውጪ

ታስረሻል የሚልሽ ወደ ሜዳው ሂጂ

ለሌላ እንዳይመስልሽ ያለ አንዳች ሀይ ባይ ሊበላሽ ነው እንጂ............

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group