Translation is not possible.

አንድ መልእክት ለዱዓት

~

በደዕዋ ላይ ላይ ከሚታዩ መሰናክሎች ውስጥ አንዱ የዱዓት አለመጣጣም ነው። ለዚህ አለመጣጣም ቀዳማዊ ምክንያት የዱዓት ነፍሲያን መከተል ነው። ለሌላ መትረፋቸው ቀርቶ ጭራሽ ሸክም መሆን። ወንድሜ! ይሄ ህዝብ ሞልቶ የተትረፈረፈ ብዙ አጀንዳ አለው። የግላችንን አመል አደባባይ እያመጣን ሌላ በሽታ አንደርብበት።

በሚያሳዝን ሁኔታ ግን አብዛኞቻችን በነፍሲያ የተተበተብን ሆነናል። "ህዝባችን ደዕዋ የተጠማ ነው፣ ደዕዋውን ለማሰናከል አድብተው የሚጠብቁ ሴረኞች ስላሉ በጥንቃቄ ተጓዙ" የሚል አደራ የተሰጣቸው ኡስታዞች አመላቸውን መግራትን እንደ ሸንፈት፣ የሌሎችን ጥንቃቄ እንደ ፍርሃት እየቆጠሩ ጅምር ስራዎችን በታትነው፣ ደዕዋውን አጠልሽተው ያርፋሉ። ብዙ ቦታዎች ላይ የሚያጋጥም ፈተና ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ ከሚታዩት ውስጥ ከፊሎቹ ከእድሜ አንፃር የወጣትነትን ግለት የተሻግሩ መሆናቸው ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በስልት ራስን መኮፈስ፣ ራስን ልዩ አድርጎ ማየት፣ ሌሎችን መናቅና ማጣጣል፣ ሌሎችን በማጣጣል የራስን ስም መገንባት ላይ መጠመድ ብዙዎቻችን ዘንድ ያለ በሽታ ነው። ወንድማለም! ራስህን ልዩ አድርገህ አትመልከት። የእውነት የደዕዋ ጉዳይ የሚያሳሳብህ ከሆንክ ደዕዋ ላይ ያሉ ወንድሞችህን እንደ አጋሮችህ፣ አጋዦችህ እንጂ እንደ ተቀናቃኝ ከመመልከት ውጣ። ሌሎችን በማጣጣል ራስን የመቆለል ቆሻ ሻ በሽታን ከልብህ አውጣ። ሁሌም ትህትናን ተላበስ። ራስህን ዝቅ አድርግ። በሆነ ነገር ከሌሎች እንደምትሻል ከተሰማህ ሌሎቹ በሌላ ነገር ካንተ እንደሚሻሉ አስብ። ሰበር ብትል የእውነትም አንተ ጋር የሌለ ብዙ መልካም ነገር ሌሎች ላይ ታገኛለህ። ራስህን በሚገባ ግራ።

በተለይ ክፍለ ሃገር ላይ ያላችሁ ዱዓቶች ከልብ አስቡበት። ደዕዋ ላይ ላሉ ወንድሞች ሞራል እንጂ ውጋት አንሁን። በዚህ ዘመን በደዕዋው ዘርፍ ላይ ያለው ምቀኝነትና ክፋት በዱንያ ጉዳዮች ላይ ከሚታየው በሽታ በጣም የራቀና የባሰ ነው። ይሄ ብንደብቀው እንኳ የማይደበቅ አሳፋሪ ግን በገሃድ የሚታይ ነውር ነው። በግል ጉዳይ በሆነ ወንድሙ ላይ ያቄመው ሁላ በደዕዋ ሽፋን ላንቃው እስኪበጠስ እየጮኸ ህዝብ ማደናገር በጣም የተለመደ ሆኗል። ወንድሜ በዚህ ዘመን ያለው እንቅፋት ብዛት በርብርብ ለመጋፈጥ እንኳ የሚፈትን ነው። ትብብሩ ቢቀር አንዱ ሌላውን ከደዕዋ መስክ ለማውጣት አለፍ ሲልም ለማጥፋት መነሳት ግን ለደዕዋው እዳ መሆን፣ ተያይዞ መክሰም ነው የሚያስከትለው። ከፍትጊያው መጨረሻ ደግሞ የሚያተርፈው ሌላ ነው። ስለዚህ ከወንድምህ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘህ ክፍተቶችን #እየተራረምክ ተደጋግፈህ ለመጓዝ ሞክር። ይሄ ካልሆነልህ ከነ ድክመቱ እያስታመሙ የሆነን ቀዳዳ እንዲሸፍን መተው የተሻለ ሊያተርፍ ይችላል። ልትሰብረው ወይም ከደዕዋው ዘርፍ አሽቀንጥረህ ልታስወጣው ከመነሳትህ፣ ልቡ ባንተ እንዲያዝን ከማድረግህ በፊት ደግመህ ደጋግመህ አስብበት።

"እኔስ ብዬሽ ነበር የዓይኔ ጉድፍ አውጪ

መዋጥ ይዘሽ መጣሽ ዓይኔን ልታወጪ!"

እንዲል አታድርገው።

.

ማሳሰቢያ፦

የማወራው ሱና ላይ (ተመሳሳይ መስመር ላይ) እንዳሉ ለሚያምኑ ዱዓት ነው።

=

Ibnu Munewor

የቴሌግራም ቻናል፦

http://t.me//IbnuMunewor

image
Send as a message
Share on my page
Share in the group