بسم الله الرحمن الرحيم
ኡለሞቻችን እና ቀደምቶቻችንን እንተዋወቅ
ኢማም አዙህሪይ رحمه الله
👉 ሙሀመድ ኢብኑ ሙስሊም ኢብኑ ኡበይዲላህ ኢብኑ አብዲላህ ኢብኑ ሺሀብ አዙህሪይ
✍ የተወለዱበት ዘመን የታሪክ ኡለሞች ብዙ አይነት ግምትን ሰጥተዋል በዚህም ተለያይተዋል 50 51 52 58 ሂጅሪያ ላይ ተወልደዋል በሚል ወደ አራት ተከፍለዋል ነገር ግን የተወለዱት በሙአዊያ ኺላፋ መጨረሻ አካባቢ እናታችን አኢሻ رضي الله عنها የሞተችበት አመት ላይ መዲና ላይ እንደተወለዱ ይገልፃሉ:
✍ ይህ ታላቅ ኢማም በጣም ድሀ ከሆኑ ቤተሰብ የተወለዱ እና በኢልም ላይ ትልቅ ጥረት እና ትግል ያደረጉ ሰው እንደሆኑ የታሪክ ኡለሞች ይናገራሉ
✍ ከዚህ ኢማም ከሚነገረው ታሪካቸው በጣም ሚገርመው ነገር በሰማንያ ለሊት ብቻ ሙሉ ቁርአንን እንደሀፈዙ ይነገራል:
✍ እንዲሁም የሀዲስ እውቀትን ከመጨረሻ አካባቢ ከነበሩት ሶሀባዎች እንደ አነስ ኢብኑ ማሊክ እና ሰህል ኢብኑ ሰእድ አሳኢዲይ እንዲሁም ሰባቱ የመዲና ፉቃሀዎች ከሚባሉት ታቢእዮች ከእነ ኡበይዲላህ ኢብኑ ኡመር እውቀት እንደያዙ ይገልፃሉ:
✍ ኢማሙ አዙህሪይ በሀዲስ ሂፍዝ መዲና ላይ ከነበሩ የሀዲስ ሁፋዝ ታቢእዮች አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው እስከ 2200 ሀዲስ ሀፍዘው እንዳስተላለፉም ይነገራል:
✍ ታላቁ የሱና ኢማም ኢማሙ አህመድ የኢማሙ ዙህሪይ ሰሂህ ከሚባል ሰነዶች ከሳሊም ከዚያም ሳሊም ከአብዲላህ ኢብኑ ኡመር ሚናገረው እንደሆነ ይገልፃል:
👉 ኡለሞች ስለ ኢማሙ አዙህሪይ ምን አሉ?
✍ ከኢማሙ አዙህሪይ ታላቅ ኢማምነት መገለጫ ኢማሙ ማሊክ እና ኢማሙ አውዛኢይ ከታላላቅ ተማሪዎቻቸው መሆናቸው ብቻ በቂ ነው:
✍ እንዲሁም ከኢማሙ ዙህሪይ ታላቅ ኢማምነት መገለጫ ኡመር ኢብኑ አብዲልአዚዝ ለተቀማማጮቹ ወደ ዙህሪይ ሂዱ በአሁን ሰአት ከአለፉት ሱናዎች ከእርሱ በላይ አዋቂ ሰው አላውቅም እያለ ወደሱ ይመራቸው ነበር በዚህም ጊዜ እነ ሀሰነልበስሪይ እና ሌሎችም ታላላቅ ኡለሞች ባሉበት ጊዜ ማለት ነው:
✍ እንዲሁም ታላቁ ታቢኢይ ሰኢድ ኢብኑ ሙሰየብ አንተን አይነት ተክቶ የሄደ ሰው ሞተ አይባልም ይላቸው ነበር:
✍ ኢማሙ ማሊክ ደግሞ በዚህ ጊዜ ኢማሙ ዙህሪይን ሚያክል በሀዲስ ዘርፍ ማንም የለም ይሉ ነበር:
✍ ኢማሙ አሻፊኢይ ደግሞ ኢማሙ ዙህሪይ ባይኖር ኖሮ ሱነኖች ከመዲና ለመጥፋት ይደርሱ ነበር ማለታቸው ይነገራል:
✍ ኢማሙ አህመድ እንዲሁም በሀዲስ እና በኢስናድ በጣም ምርጥ ከሚባሉት ዋናው ኢማሙ ዙህሪይ ነው ብለዋል:
✍ አሊይ ኢብኑ አብዲላህ አልመዲኒይ በሰባቱ የታቢኢይ ፉቃሀዎች ንግግር ይበልጥ አዋቂ እንደ ዙህሪይ የለም ብለዋል:
👉 ኢማሙ አዙህሪይ ለእውቀት ፈላጊዎች ካስቀመጧቸው ምክሮች 👇👇
1 እውቀትን መያዝ የፈለገ በደረጃ ደረጃ ከትንሽ ወደ ትልቅ እየያዘ ይሂድ እንጂ ሁሉንም በአንዴ ለመያዝ የፈለገ ሰው በእራሱ ላይ ሚከብድን ነገር እያከማቸ ነው እንጂ እውቀትን አይሰበሰብለትም ይሉ ነበር:
2 እውቀትን የፈለገ ሰው ወደ ኡለማዎች ይሂድ እንጂ ኡለማዎች ወደ እውቀት ፈላጊው ቤት እየዞሩ ማስተማር የለባቸውም ይል ነበር ምክንያቱም ኡለሞች ወደ እውቀት ፈላጊው መሄዳቸው እውቀትን ማሳነስ እና ማዋረድ ነው ይሉ ነበር:
روي عن مالك أنه قال: سمعت الزهري يقول: هوان العلم وذله أن يحمله العالم إلى بيت المتعلم.
ታላቅ የሆኑ ተማሪያቸው ከሳቸው ይህን ንግግር እንዳስተላለፉ ይነገራል
3 በደርስ ላይ ወይም መጅሊስ ላይ ጊዜ መርዘምን ይጠሉ ነበር ምክንያቱም ይህ ለስልቹነት እና በማይቻል እና በማይሆን ነገር ውስጥ መስመጥን ያመጣል ይሉ ነበር እንዲሁም ከንግግራቸው አንድ ቦታ ላይ መጅሊስ አይረዝምም ከዚያ መጅሊስ ለሸይጧን ድርሻ ቢኖረው እንጂ ይሉ እንደነበር ከተማሪዎቻቸው ይነገራል:
4 ሂፍዝ መሀፈዝ ላይ ያለ ሰው ዘቢብ መብላት እና ንፁህ ማርን መጠጣት ለማስታወስ ፍቱን መድሀኒት እንደሆኑ ለተማሪዎቻቸው ይመክሩ እንደነበር ይነገራል:
ይህ የታላቁ ኢማም አሊም ኢማም አዙህሪይ ታሪክ እና ማንነት በአጭሩ ሲሆን ማንም በዚህ ምድር ሚቀር የለምና ይህም ታላቅ ሰው ይህቺን ሀያት አዱንያን በኸይር አሳልፈው የተለዩዋት ማክሰኞ ለሊት በረመዳን አስራ ሰባተኛ ቀን ከሂጅራ 124 ላይ ነበር
رحمه الله رحمة واسعة واسكنه فسيح جناته