የሀገሪቷ ባለቤት ግን ማን ነበር?... ፍልስጤማውያን ወይስ እስራኤላውያን?
****
እውነቱን ማወቅ የሚሻ ሰው ፡ ፅሁፉን ታግሶ ያንብበው!🙏
🇵🇸🇵🇸🇵🇸#ሠላም__ለፈለስጢን??????
ብዙ የታሪክ መፅሐፎችን በመፃፍ የሚታወቁት የታሪክ ፀሐፊው አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ ፡ "የህይወቴ ታሪክ" በሚለው ግለ ታሪክ መፅሐፋቸው ውስጥ ፡ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን ስለሚጣሉበት የመሬት ጉዳይ ፅፈዋል። መሬቱ ከጥንት ጀምሮ የማን እንደነበረም በፅሁፋቸው ውስጥ ገልፀዋል።
ከግለ ታሪክ መፅሐፋቸው የተወሰደውን ሀሳባቸው እነሆ፦
<<...በመፅሐፍ ቅዱስም ፡ በሌላውም ስጋዊ ታሪክ እንደተፃፈው ፤ አሁን አረብና እስራኤል የሚፋጁበት አገር ምድር ፡ የከነአናውያን አገር ናት። ከነዓናውያን ማለትም ሲዘረዘር፦ ፍልስጤማውያን ፣ አማሌቃውያን ፣ ኤዶማውያን እና አሞናውያን የሚባሉት ናቸው። በነዚህ መካከል ከኡር (ከኢራክ) አብርሃም ስደተኛ ሆኖ መጥቶ ተቀመጠ ፤ ይስሐቅን ወለደ ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ፤ ያዕቆብም 12ቱን የነገድ አባቶች ወለደ። ከዛ በኋላ ወደ ግብፅ ከነቤተሰቡ ሄዶ በዚያም የእርሱ ዘር በአራት መቶ አመት ውስጥ እየተበራከቱ ከሄዱ በኋላ ፡ ይህ የበረከተው የአንድ ቤተሰብ ዘር ከግብፅ ተሰዶ ወደ ከነዓናውያን አገር ተመልሶ መጣ።
ይህ ህዝብ በግብፅ ሲኖር ሰልጥኖ ነበርና ያልሰለጠኑትን የከነዓንን ህዝብ በቀላሉ አሸንፎ ገባና የመዠመሪያውን መንግስቱን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ14ኛው መቶ አመት አቋቋመ። በጥንታውያኑ ባለቤቶችና ባዲስ መጦቹ ህዝቦች መካከል ጦርነቱ ምንግዜም እንዳልቆመ መፅሐፍ ቅዱስ ይዘረዝርልናል። ከሁሉም ነገድ የበለጠ [መጤዎቹን] የተቋቋሙት የፍልስጤም ህዝቦች ናቸው። እነዚህም ዙሪያውን ሆነው ሲታገሉ ኖሩ።
ነገር ግን በተለይም ከሳኦል ወዲህ በዳዊትና በልጁ ሰለሞን ጊዜ እስራኤሎች በርታ ብለው ከቆዩ በኋላ ፡ ከዚያው ከጎናቸው የባቢሎንና የአሶራውያን ፡ ቀጥሎም የፋርስ ነገስታት እየወረሩ እስራኤሎችንም ፍልስጤሞችንም ይገዟቸዎ ጀመር። ከፋርሶች ግሪኮች ፡ ከግሪኮች ሮማውያን በገዥነት ቀጠሉ። እስራኤሎቹ ለሮማውያን አንገዛም ብለው ስለሸፈቱ ፡ ቲቶስ የሚባለው የሮማውያን ጄነራል ምሽጋቸውን አፈራርስ በያሉበት በታተናቸው።.... ፍልስጤማውያን ግን ለሐይለኛው እየተገዙ ሳይበተኑ እዚያው ስለኖሩበት ፡ የጠቅላላው የአገሪቱም ስም... ፍልስጤም ይባል ጀመር!....
[በየቦታው] የተበተኑት ይሁዲዎች ፣ የሄዱበትን አገር ዜግነት እየተቀበሉ ፣ እየተማሩ ፣ እየነገዱ ፣ እየተሾሙ ፣ እየከበሩ ፣ አንዳንድ አገር ላይም መሪ እስከመሆን ደርሰዋል።... ፓለስቲኖች [ፍልስጤማውያን] ግን ከአራት ሺህ አመት ዘመን ጀምሮ የኖሩበትን አፈር ሳይለቁ ስለኖሩ ፡ እንደባላጋራዎቻቸው በእውቀት የመሠልጠን እድል አላገኙም። ስለዚህ ይሁዲዎች በያሉበት አገር ፡ ያሉበት አገር በሰጣቸው የነፃነት መብት እየተጠቀሙ ፣ በማህበር እየተዘጋጁ ፣ በአንደኛው የአለም ጦርነት ፍፃሜ ፡ አሸናፊው እንግሊዝ ከተሸናፊው ቱርክ እጅ ፓለስታይንን ወስዶ በሚያስተዳድርበት ዘመን ፡ [አይሁዶች] ወደ ፓለስታይን እየገቡ ቀስ በቀስ ከሞኙ አረብ መሬት እየገዙ መቀመጥ ጀመሩ። እ.አ.አ በ1917 ዓ.ም. የገዥው የእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር "ይሁዲዎች በፓለስታይን አንድ መኖሪያ ማግኘት አለባቸው" ብሎ ተስፋ ሰጠ። በዚህን አመት በፓለስታይን ካለው ጠቅላላ ህዝብ ፡ ይሁዲዎች 8% ሲሆን ፡ 92%ቱ የፓለስቲን ተወላጆች ናቸው። ከዚህ በኋላ ግን ይሁዲዎች በየአመቱ የነበሩበትን የአውሮፓ አገር እየለቀቁ ፡ በስደት ወደ ፓለስቲን እየገቡ ፡ በየጊዜው ቁጥራቸው እየበረከተ ሄደ።....
ይሁዲዎች በማናቸውም የአለም መንግስታት ውስጥ በሐብትም ፡ በጋዜጣና በፕሮፖጋንዳ መርጨትም ፡ ከፍተኛ የቁጥጥር ችሎታና ሀይል ስላላቸው ፡ በፖለቲካ መስክ የማይቻሉ ሆኑ። እንግሊዝም.... ጓዙን ጠቅልሎ [ከፍልስጤም ምድር] ሲወጣ ፤ በየአገሩ በወታደርነትና በቴክኒክ የሠለጠኑት ይሁዲዎች ፣ ከአገር ያልወጡትን እና እንደነርሱ ያልሰለጠኑትን ፓለስቲኖችን በወታደራዊ ሀይል እያወደሙ ፣ ከየመንደራቸውም እያባረሩ ገቡበት። የፓለስቲኖችም እድል ፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ፡ ለእስራኤሎች መገዛት ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር ተሰዶ በበረሀና በድንኳን መኖር ሆነ።....
ከስራ ሰአት ውጭ ወይም ቅዳሜና እሁድ ፡ በእየሩሳሌም ፡ ከዚያም ራቅ ብዬ በጋዛ ከተሞች እየተዘዋወርኩ ስጎበኝ ፣ "ይህ ህንፃ የማነው?" ስል ፡ ቀድሞ የፓለስቲን ተወላጅ እንደነበረ ፡ አሁን ግን ከአውሮፓ ፣ ከጀርመን ፣ ከፖላንድ ወይም ከመስኮብ የመጣ ይሁዲ እንዳለበት ፣ ባለቤቱ [ፍልስጤማዊ] ግን... ተሰዶ በሶርያ በርሃ በድንኳን ውስጥ እንደሚኖር በብዛት ተረዳሁኝ። ወደ ጆርዳን ተሻግሬ ፡ ኢያሪኮ አጠገብ ያለውንና በበረሃ የታመቀውን [የፍልስጤም] የስደተኛ ብዛት ፣ የሽሚግሌውን ፣ የህፃኑን ፣ የወንድና የሴቱን አኗኗር አይቼ በመንፈሴ ተበሳጨሁኝ። በአለም ላይ የእውቀት ፣ የገንዘብና የጉልበት ሀይል እንጂ ፣ ትክክለኛ ህግ ፡ እውነትና ፍትህ እንደሌለ ፡ ቀድሞ የማውቀው የበለጠ እየተብራራልኝ ሄደ።
ከከተሞች ወደ ወረዳዎች ፤ ወደ ናዝሬት ፣ ወደ ገሊላ ፣ ወደ ቃና ፣ ወደ አሽቅሎን ፡ ለእረፍትና ለሽርሽር እያስመሰልኩ በምዘዋወርበት ጊዜ ፣ ብዙ የፓለስቲን የለሙ የወይንና የወይራ ፍሬ እርሻዎች ፡ ከአውሮፓ በመጡ ይሁዲዎች እጅ ተይዘው ፣ ባለቤቶቹ ፓለስቲኖች ግማሾቹ ወደ ስደት ሄደዋል ፤ ወደ ስደት ያልሄዱት ፓለስቲኖች ደግሞ ፡ ለይሁዲዎች ወይም ለመንግስት እንደ ጭሰኛ ሆነው ይሰራሉ።.... አያት ቅድመ አያቶቻቸው በኖሩበት ፣ እነሱም ተወልደው ባደጉበት አገር ፡ ከአውራጃ ወደ አውራጃ ያለፈቃድ ሊዘዋወሩ አይችሉም። በትውልድ አገራቸው ፡ ከውጭ ለመጣው ይሁዲ ተገዥ ሆነዋል።....
እኔ ይህን ሁሉ በመመልከት ፣ መንፈሴና ህሊናዬ ለፓለስቲኖች ሲያደላ ፤ እኔ ወኪል የሆንሁበት የዛን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ከእስራኤል ወገን ቆሟል።>> በማለት የሚያውቁትን እውነታን በምስክርነት መልክ በመፅሐፋቸው ውስጥ አስፍረውታል።
አቶ ተክለፃድቅ መኩሪ በንጉሱ ዘመን በእስራኤል የኢትዮጵያ ቆንስል ሆነው ሰርተዋል። በዚህም ምክንያት በእስራኤልና በፍልስጤም ዙሪያ ያለውን ጉዳይ በአካል የማየት እድሉን አግኝተዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ከፍልስጤምና ከእስራኤል ግጭት ጋር የሚገናኙ ብዙ ዶክመንቶችን የመመርመር አጋጣሚንም አግኝተው ብዙ ዶክመንቶችን መርምረዋል። ብዙ ከመረመሩና ካስተዋሉ በኋላም ፡ የፍልስጤማውያንን መበደልና መሰቃየትን ተረድተው በመንፈስ የፍልስጤም ደጋፊ ሆነዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በመፅሐፋቸው ውስጥ ያሰፈሩትን ተጨማሪ ሀሳቦችን ማወቅ የምትሹ ከሆነ ፡ "የህይወቴ ታሪክ" የተሰኘውን ግለ-ታሪክ መፅሐፋቸውን ከገፅ 173 _ 182 ድረስ ያሉትን ገፆች ታነቡ ዘንድ እጋብዛለሁኝ።
ይኸው ነው!🙏
🇵🇸 #ድል_ለፈለስጢን??
#ሠላም__ለፈለስጢን??